አርብቶ አደሩ በፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ተካቶ ህይወቱን እንዲያሻሽል እየተደረገ ነው -የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አርብቶ አደሩ በፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ተካቶ ህይወቱን እንዲያሻሽል እየተደረገ ነው -የግብርና ሚኒስቴር

አርባ ምንጭ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ)፡- አርብቶ አደሩ በፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ተካቶ ህይወቱን እንዲያሻሽል እየተደረገ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን በአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የአርብቶ አደር ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮጀክት አፈጻጸም ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ መክሯል።
በግብርና ሚኒስቴር የድርቅ መቋቋሚያና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻል ፕሮግራም ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ጀማል ዓሊ እንደገለጹት በአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮጀክት የአርብቶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በፕሮጀክቱ አርብቶ አደሩ በድርቅ ጊዜ መኖ በመግዛት እንስሳቱን እንዲታደግ፣ በግብይት እንቅስቃሴ ከእንስሳቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ እንዲሁም የባንክ ቁጠባና ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ኑሮውን በዘላቂነት እንዲቀይር ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የአርብቶ አደር አካባቢዎች በስፋት ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመው በ5 ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮች የኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለዚህም ከዓለም ባንክና ከኢትዮጵያ መንግስት 117 ሚሊየን ዶላር የተመደበ ሲሆን በቀጣይ 13 ሚሊየን የሚጠጉ አርብቶ አደሮችን በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አቶ ጀማል ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ በበኩላቸው የክልሉ ሰፊ አርብቶ አደሮች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በየጊዜው ለአደጋ እየተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ 11 ሺህ 168 አባወራና እማወራ አርብቶ አደሮችን ለማቋቋም ከ52 ሚሊየን ብር በላይ ጥቅም ላይ መዋሉንም አስታውስዋል፡፡
አርብቶ አደሩ ከድርቅ አደጋ በተጨማሪ የእንስሳት የግብይት ስርአቱ ባለመዘመኑ ከእንስሳት ሀብቱ ተገቢውን ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ታምርሶ ናቸው፡፡
ኢጀንሲው አርብቶ አደሩን በማደራጀትና ግንዛቤ በመፍጠር የባንክ ቁጠባና ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆንና በግብይት ስርአቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ኮሚሽን፣ ህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ፣ ከሴቶችና ህፃናት፣ ከፋይናንስ፣ ከመንገድ ልማት ቢሮና ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡