የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ በቅድመ ምረቃ የዲግሪ መርሐ ግብር የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎችን ሰኞ ይቀበላል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ  በቅድመ ምረቃ የዲግሪ መርሐ ግብር የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎችን በመጪው ሰኞ እንደሚቀበል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ600 በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።

በአብራሪነት 88 ፣ በበረራ መስተንግዶ 150፣ ማርኬቲንግ 264 እና በአውሮፕላን ጥገና 125 በድምሩ  627 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።

ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ከአፍሪካ አገራት የመጡ ናቸው።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ካሴ ይማም፤ በምርቃት ስነ-ስርአቱ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲው ቀደም ሲል በአካዳሚ ደረጃ በርካታ የአቪየሽን ባለሙያዎችን ሲያሰለጥን ቆይቷል።


 

ለአቪየሽን ዘርፉ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ በማስፋት ከዚህ ዓመት ጀምሮ በሶስት የቅድመ ምረቃ የዲግሪ መርሃ ግብሮች ተማሪዎችን እንደሚያሰለጥን ጠቅሰዋል።

በዚህም ዩኒቨርሰቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በቅድመ ምረቃ የዲግሪ መርሐ ግብር ተማሪዎችን ሰኞ ታህሳስ 1/2016 ዓ.ም  ይቀበላል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በአቪየሽን ማናጅመንት፣ በዴታ ሳይንስ በሁለተኛ የዲግሪ መርሐ ግብር ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት መጨረሱን ተናግረዋል። 

አቪየሽኑ ቀደም ሲል በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሙያተኞችን ሲያሰለጥን የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከኤስያ ሀገራት፣ ከሩሲያና ሌሎች ሀገራት ሰልጣኞች እየመጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

በንድፈ ሃሳብ የተሰጠውን ትምህርት በተግባር ለማሰልጠን የተሟላ ቁሳቁስ መኖሩ አቪየሽኑን ተመራጭ እንዳደረገው ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የሚሰጠውን ትምህርትም ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው አየር መንገዱ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ መንገደኞችንና የዕቃ ጭነትን የማጓጓዝ አቅሙን እየጨመረ ነው ብለዋል።


 

ከዚህም ባለፈ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የሚጠግንና የራሱን የሰው ሀይል በራሱ ማስተማርና ማብቃት የሚችል ግዙፍ የአቪየሽን ኩባንያ መሆኑንም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ 145 አውሮፕላኖችን በመያዝ በአለም አቀፍ ደረጃ 135  ከተሞችን መዳረሻ በማድረግ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።

ከፍተኛ ሀብት ካላቸውና በቴክኖሎጂ ከዘመኑ አየር መንገዶች ጋር ተወዳድሮ በትርፋማነትና በእድገት መቀጠሉን በማንሳት።

የድርጅቱ መሪዎች ራዕይና ዕውቀት፣ የሰራተኞች በታታሪነትና በቁርጠኝነት ማገልገል  አየር መንገዱ አሁን ለደረሰበት የስኬት ምዕራፍ ትልቅ ሚና ማበርከቱን ጠቅሰው፤ ተመራቂ ተማሪዎች የድርጅቱን እድገት ለማስቀጠል በቁርጠኝነትና በጥንካሬ የመስራት ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም  ተመራቂዎች ለበረራ ደህንነት፣ ለደንበኞች አገልግሎት፣ ለመልካም የስራ ባህልና ራስን ማብቃት ትኩረት እንዲሰጡም ነው ያሳሰቡት።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎች በበኩላቸው በተማሩበት የሙያ መስክ አገራቸውንና ድርጅቱን በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከተመራቂዎች መካከል ከታንዛኒያ የመጡት አይሻ ሞሃመድና እና አዩቡ ኬዲሙንዲ በአቪየሽን ዩኒቨርስቲው ያገኙት እውቀት ህልማቸውን እውን ለማድረግ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም