በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፦በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና ዘርፉን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታትና ዘርፉን የበለጠ ለማነቃቃት ትኩረት አድርጎ ያዘጋጀው ፎረም አዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በፎረሙ ላይ የዘርፉ የፌደራልና የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መስፍን ነገዎ፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የግንባታ ጥራት መጓደል፣ የግብዓት እጥረት፣ የግንባታዎች በወቅቱ ያለመጠናቀቅ፣ የግብዓት የዋጋ ንረትና ሌሎችም ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ ከፖሊሲ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ናትናኤል ጌታሁን በበኩላቸው፤ በክልሉ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን ዕድገት ለማፋጠን ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን በመደገፍ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ስራዎች በመታገዝ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የግዥ ስርዓትን በማዘመን፣ ግልጽነትን በማስፈን ጥራት ያለው መሰረት ልማት እንዲኖር ጥብቅ ክትትል ማድረግም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል።

በኮንስትራክሽን መስኮች ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶች መካከል  አቶ አብዲሳ እሸቱ ከግንደበረት ኮንስትራክሽን ፣አቶ ተስፋሁን ኢሳያስ ከቪክቶር ዶርስና አቶ ዮናስ ሙሉጌታ ከዮት ኮንስትራክሽን በሰጡት አስተያየት፤ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ ቢመጣም አሁን ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በግብዓት ላይ የሚስተዋል ገበያ ዋጋ አለመረጋጋት፣ የግብዓት እጥረት እና ሌሎችም ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ መንግስት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ ለመንግስት ብቻ የሚሰጥ ስራ እንዳልሆነ ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ሁሉም ባለሃብት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም