በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል እየተሰራ ነው  

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፡-  በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የሚከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ። 

ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባለሥልጣኑ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ የኃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ሥርጭትን ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጫ ነው።

አሁን ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ በአንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚተላለፉ የኃሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች አብሮነትን የሚሸረሽሩ ግለሰቦችን ለተሳሳተ ውሳኔ የሚያጋልጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም እነዚህን ድርጊቶች ለመከላከል በተለይም ታዳጊ ተማሪዎች ኃሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮችን የመለየት ክህሎትን በመጨበጥ እንዳይሰራጭ በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት። 

ባለሥልጣኑ ያዘጋጀው ሥልጠናም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይህንን እንዲያውቁና እንዲከላከሉ ማስቻል መሆኑን ተናግረው ሥልጠናው በቀጣዮቹ ጊዜያትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

ራስን ከጥላቻ በማጽዳት አብሮነቷ የጎለበተ አገር መገንባት እንደሚገባ ገልጸው በዚህ ሂደት በተለይም ወጣቱ ትውልድ ለአገር ግንባታ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።


 

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የቦሌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ  መክሊት ገዛኸኝ ሥልጠናው ያለብንን ድክመቶችና የአጠቃቀም ችግሮችን እንድናውቅ አግዞናል ብላለች።


 

ሌላኛው የዚሁ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ጸጋዬ ድረስ በበኩሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ መረጃዎችን እውነተኛነት እንዴት መለየት እንደሚቻል በሥልጠናው ለመመልከት መቻሉን ገልጿል።

በተለይም መረጃዎች ምንጫቸውን እንዴት ማወቅ እንደሚቻል ለመገንዘብ መቻሉን ተናግሯል።


 

መሰል ሥልጠናዎች በየጊዜው መስጠት እንዳለባቸው የገለጸችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የደጅ አዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ሁለተኛና አጠቃላይ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሃና ዘውዱ ናት።

የኃሰተኛ መረጃዎች ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር የሚደርስ ብዙ ጉዳት እንደሚያመጣ ገልጻ ይህንን ለመከላከል እንደምትሰራ አረጋግጣለች።

ሥልጠናው በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል። 

ሥልጠናው በዋናነት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ምንነት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ባህሪያት፣ እውነትን ማጣራት የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል። 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም