አትሌት ለተሰንበት ግደይ የዓለም አትሌቲክስ ኢንተርናሽናል ፌርፕሌይ ሽልማትን አሸነፈች - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት ለተሰንበት ግደይ የዓለም አትሌቲክስ ኢንተርናሽናል ፌርፕሌይ ሽልማትን አሸነፈች

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016(ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያዊቷ የረጅም ርቀት አትሌት ለተሰንበት ግደይ የዓለም አትሌቲክስ ኢንተርናሽናል የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት አሸናፊ መሆኗ ይፋ ተደርጓል።
የአለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የአለም ፌር ፕለይ ኮሚቴ በጋራ ባደረጉት የመጨረሻ ምርጫ አትሌት ለተሰንበት ግደይ አሸናፊ መሆን ችላለች ።
አትሌቷ በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 10 ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር ላይ የውድድሩ መጨረሻ ላይ ትራክ ላይ ወደ ወደቀችው ኔዘርላንዳዊት አትሌት ሲፋን አሰን በመሄድ ያሳየችው ስፖርታዊ ጨዋነት በኮሚቴው እና በተመልካቾች ምርጫ እንድታሸንፍ ማስቻሉን በመረጃው ተመልክቷል።
አትሌት ለተሰንበት ግደይ ከሽልማቱ በኋላ በሰጠችው አስተያየት፤ " አትሌት ሲፋን ሀሰን ስትወድቅ ከልቤ አዝኜ ነበር ምክንያቱም ስሜቱን አውቀዋለሁ ብላለች፡፡
የ2023 የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት በማሸነፌ ተደስቻለሁ ማለቷን ከአለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።