የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ህዝቦች ይበልጥ እንዲተዋወቁ ማስቻሉን የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ

መቱ/ ነቀምቴ፤ሕዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፦ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር  ህዝቦች ይበልጥ እንዲተዋወቁ፣ አንድነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከር  እድል እየፈጠረ ነው ሲሉ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ባከበሩበት ወቅት በዓሉ የሕዝቦችን ወንድማማችነት እያጠናከረ ነው ብለዋል።

ተማሪ ኬን ኩዌስ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ዜጎች ይበልጥ እንዲተዋወቁና እንዲከባበሩ እድል ፈጥሯል ብላለች።

''ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች መጥተን ተከባብረንና ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ጠብቀን እየተማርን ነው'' ያለቸው ተማሪ ኬን ''በዓሉ አንድነታችንን ለማጠናከር አግዞናል'' ስትልም ገልጻለች።

ተማሪ ፈትያ መኪ ሰይድ በበኩሏ ለኢትዮጵያ ሰላምና ዕድገት እውን መሆን ለልዩነቶቻችን እውቅና የመስጠት እንዲሁም የመከባበር፣ አብሮነትን ማጎልበት ይገባል ብላለች።

ለዚህ ደግሞ እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ያሉ የጋራ ጉዳዮቻችንን ማሳደግ የሚያችሉ መድረኮች ወሳኝና ይበልጥ የመተዋወቂያና መቀራረቢያ መድረኮች መሆናቸውን ተናግራለች።

ዩኒቨርሲቲዎች ከተለያዩ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የኃይማኖትና ሌሎች ብዝኃነቶች የመጡ ተማሪዎች ለዓመታት በጋራ የሚቆዩበት እንደመሆኑ ለኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የተናገረችው ደግሞ ተማሪ ሲፈን ድሪባ ናት።

በተለይ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መከበሩ ትልቅ ትስስር የሚፈጥር መሆኑን ተናግራለች።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ኩምሳ ታምሩ በበኩሉ ''በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልዩነቶቻችንን አክብረንና አንድነታችንን ጠብቀን የምናሳልፈው ጊዜ ለኢትዮጵያዊ አንድነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው'' ብሏል።

የብሔር ብሕረሰቦች ቀን መከበሩ ለእኩልነት፣ ለአንድነት፣ ለአብሮነት፣ ለትውውቅና ለወንድማማችነት መጠናከር ትልቅ ዕድልን የፈጠረ ነው ሲልም አክሏል። 

በተመሳሳይ የወለጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዓሉን አክብረዋል።


 

የበዓሉ ተሳታፊ ተማሪዎች፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ውበታችንን የምናጎላበትና አንዱ ሌላው የሚያውቅበት ነው ብለዋል።

ተማሪ ገመቺስ ታከለ፣ የሌላውን ማንነት ማክበር ራስን ማስከበር መሆኑን ገልጻ ሁሉም ተቻችሎ እና ተከባብሮ አገሩን ማሳደግ አለበት ብላለች።

ተማሪ መለሰ ያእቆብ በዩኒቨርሲቲው እርስ በርስ ተከባብረው ያለችግር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጿል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር እኩልነትና ብዝሃነት ማስተዋወቅ መሆኑን አስረድተዋል።

የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብም በፍቅርና በመከባበር የተሻለ ዜጋ የማፍራቱን ስራ ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በወለጋ ዩኒቨርስቲ 18ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ላለፉት አምስት ቀናት በተለያዩ ፕሮግራሞች ሲከበር መቆየቱም ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም