አሲዳማ አፈርን በኖራ አክመን በማልማት ውጤታማ አድርጎናል

ጂንካ፤  ህዳር 29 /2016 (ኢዜአ) ፡- አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ማልማት መቻላቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰሜን አሪ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ  አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በወረዳው ጋሲና-ዘማ፣ አይካ ሰልሚ፣ ዞፍና ዳዋና ሻማ ቡልቄት ቀበሌዎች በ45 አርሶ አደር ማሳ ላይ  በአሲዳማ አፈር ላይ በሙሉ ፓኬጅ በሙከራ ደረጃ የለማ የገብስና የስንዴ ማሳ ተጎብኝቷል።

የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል የሰብል ተመራማሪዎች ባለፉት አራት ወራት በወረዳው አራት ቀበሌዎች በሙከራ ደረጃ የስንዴና የገብስ ምርጥ ዘርን ከኖራና፣ ከአፈር ማዳበሪያ ጋር በማዋሀድ በኩታ ገጠም በ10 ሄክታር ላይ የማላመድ ስራ ማከናወናቸው ተመልክቷል።

በምርምር ሂደቱ ኖራን ከአፈር ማዳበሪያ ጋር በማዋሀድ የተዘራው ሰብል መሬቱ ያለውን አሲዳማነት በመቋቋም ከአካባቢው የሰብል ዝርያዎች በእጥፍ ምርት መስጠቱ ተረጋግጧል።

በወረዳው በጋሲና ዘማ ቀበሌ በተደረገው ምልከታ በስንዴና በገብስ ልማቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ውስጥ ጋስካ ክፍሌ በሰጡት አስተያየት አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም በሙከራ ደረጃ ማልማት የጀመርነው የሰብል ልማት ውጤታማ አድርጎናል ብለዋል።

የእርሻ ማሳቸው አፈር አሲዳማ በመሆኑ ለሰብል ስለማያመች የልማት ስራቸውን አስቸጋሪ አድርጎባቸው እንደቆየ ተናግረዋል።

የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከልና የግብርና ባለሙያዎች አሲዳማ አፈሩን በኖራ በማከም ስንዴና ገብስ ማልማት እንደምንችል ሲነግሩን ለማመን ተቸግረን ነበር ያሉት አርሶ አደሩ፤ባለሙያዎቹ በተግባር ሲያሳዩን በጣም ተደንቀናል ሲሉ ገልጸዋል።

አርሶ አደር ኤፍሬም ጥጋቤ "በማሳችን አሲዳማ አፈሩን በኖራ በማከም በሙከራ ደረጃ ያለማነው የገብስና የሰንዴ ሰብል ከዚህ ቀደም ከምናለማቸው ሰብሎች አሲዳማነቱን በመቋቋም በእጥፍ ምርት አግኝተናል" ብለዋል።

የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ ማድረጋችን ውጤታማ አድርጎናል ያሉት አርሶ አደሩ፤ ከዚህም ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም በቀጣይ በስፋት በማልማት ኑሮአቸውን ለመለወጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የተሳተፉት አርሶ አደር ፅንገና ጋራ በበኩላቸው፤ ያዩትን ልምድና ተሞክሮ ወደ አካባቢያቸው በማስፋት   ለማልማት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር  ዶክተር ተክሌ ዮሴፍ፤ ማዕከሉ በጥናትና ምርምር  በማስደገፍ በአካባቢዊ ያለውን የሰብል፣ የ"ሆርቲካልቸር" እና የእንስሳት ሀብት ምርታማነት በማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሮችን ኑሮ ለመለወጥ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ማዕከሉ ላለፉት አራት ወራት በሰሜን አሪ ወረዳ ሁለት ክላስተሮች አሲዳማ አፈሩን በኖራ በማከም በ45 አርሶ አደሮች ማሳ በ10 ሄክታር ላይ ስንዴና ገብስን በኩታ ገጠም ሲያለማ መቆየቱን አውስተዋል።

"በሙከራ ሂደቱ የአበረታች ውጤት መገኘቱን አመልክተው፤  ከዚህ ቀደም ምንም ምርት የማይሰጡ መሬቶች ምርት መስጠት ጀምረዋል" ብለዋል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም ግፋ ቢል ከአንድ ሄክታር ሁለትና ሶስት ኩንታል ምርት ያገኙ እንደነበር ጠቅሰው፤  በምርምር ማዕከሉ የምርምር ስራ  እስከ 50 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደሚቻል መረጋገጡን ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቱዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ያሲን ጎኣ በበኩላቸው፤ በምርምር ማዕከሉ የተገኙት ውጤቶች የተጀመረውን የስንዴ ልማት የማስፋፋት ስራን የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"በእጃችን ያሉ የተፈጥሮ ፀጋዎች አሟጠን በማልማት የአርሶና አርብቶ አደሮችን ህይወት ለመለወጥ በቁርጠኝነት በመስራት ሁሉም መሬቶች መልማት አለባቸው" ብለዋል።

የግብርና ምርምር ማዕከላት በሰብል፣  በ"ሆርቲካልቸር" እና በእንስሳት ሀብት ምርታማነትን በእጥፍ የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማላመድና በማስፋፋት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጀመሩትን ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በምርምር የተገኙ ውጤቶችን በማስፋት የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል እንሰራለን ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ግዳልቅ አልቅሚ ናቸው።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኘው መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን አንስተው፤ ኖራ በስፋት በማቅረብ አፈርን እያከሙ ለማልማት መታቀዱን አንስተዋል።

በጉብኝቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ አርሶ አደሮች፣ የክልልና የዞን የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም