በጅግጅጋ ከተማ ሲከበር የነበረው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በሰላም ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጅግጅጋ ከተማ ሲከበር የነበረው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በሰላም ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፡- በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት ሲከበር የነበረው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በሰላም መጠናቀቁን የሶማሌ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈርሃን ጅብሪል ለኢዜአ እንደገለጹት 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ለተከታታይ ቀናት በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት ሲከበር ቆይቶ በሰላም ተጠናቋል።
በበዓሉም ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ የባህል ቡድኖች በጅግጅጋ ከተማ ባህላዊ ትርኢት በማቅረብ ልምድና ተሞክሯቸውን የተጋሩበትና በደስታ ያሳለፉበት ቆይታ እንደነበርም ነው የገለጹት።
ዝግጅቱም ያማረና ያለአንዳች የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ለነበራቸው የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት፣ ለጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎችና ተባባሪ አካላት ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
የመገናኛ ብዙኃንም በበዓሉ ላይ መታደም ያልቻሉ በአገር ውስጥና በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲደርስ ለማድረግ ላደረጉት ርብርብ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም እንግዶች በጅግጅጋ ከተማ የነበራቸውን አስደሳች ቆይታ አጠናቀው ወደየመጡበት አካባቢ በሰላም እንዲደርሱ ሽኝት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል "ብዝኅነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
ባለፉት የኅዳር-25፣ 26፣ 27፣ 28 እና 29/2016 ዓ.ም በቅደም ተከተል "የወንድማማችነት፣ የብዝኃነት፣ የአብሮነት፣ የመደመር እና የኢትዮጵያዊነት" ቀናት በተለያዩ ደማቅ ሥነ-ስርዓቶች ተከብሮ ፍፃሜውን አግኝቷል።
በዛሬው የማጠቃለያ መርሃ-ግብርም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል ቡድኖች ታድመዋል።