የመንግሥት ተቋማት የአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ የሚያደርግ አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፡-  የመንግሥት ተቋማት የአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ የሚያደርግ አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ የግልና የማኅበራት አምራች ኢንዱስትሪዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል። 


 

በዚህም የቡልኮ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር፣ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ፣ የፎንተኒና ቆዳ ፋብሪካ፣ የአዳል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል የወረቀት ፋብሪካና የኢትዮጵያ ልህቀት ማዕከል ተጎብኝተዋል።

ከመስክ ምልከታው በኋላ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ "ኢትዮጵያ ታምርት" የሚል ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።

"በኢትዮጵያ ታምርት" እንቅስቃሴ ምርት በስፋት እንዲመረት ከማድረግ ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት።

በማምረት አቅማቸው ዝቅ ብለው የነበሩትን ደግሞ የመደገፍ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

አሁን ደግሞ የአገር ውስጥ ምርትን በአገር ውስጥ የመጠቀም ባህልን ለማሳደግና ዘርፉን በማጠናከር አገሪቱ ከመስኩ ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። 

ይህንንም ተከትሎ በተለይም የመንግሥት ተቋማት የአገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀሙ አቅጣጫ መቀመጡን ነው ያስረዱት። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አማረች ባካሎ በበኩላቸው የመስክ ምልከታው በሪፖርት የቀረበልንን መሬት ላይ መኖሩን እንድናረጋግጥ አስችሎናል ብለዋል።


 

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራት እያከናወነ መሆኑንም መመልከታቸውን ጠቁመው በቀጣይም እነዚህ ተግባራት መጠናከር አለባቸው ነው ያሉት።

ቋሚ ኮሚቴው ለዘርፉ ተዋናዮች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ ይሰራል ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም