ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ድጋፋችንን እናጠናክራለን

ሶዶ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፡-  ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሚሽኑ ተባባሪ አካላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለተባባሪ አካላት ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል።

በዚሁ ጊዜ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋሞ ዞን የተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ወንድሙ ኡቶ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ለኮሚሽኑ ቀጣይ ተግባራት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ገልፀዋል። 

ምክክሩ በሀገራችን ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸው ምክክሩ የህዝብ የፖለቲካና መሰል ጥያቄዎች እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት አስረድተዋል።

በምክክሩ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን በማስተባበር እንደተባባሪ አካል የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። 

በቀጣይ ኮሚሽኑ በሚኖረው ተግባራት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል። 

በክልሉ የጋርዱላ ዞን ነዋሪ ወይዘሮ ዘርትሁን ኩሴ በበኩላቸው "ተባባሪ አካል እንደመሆኔ በዚህ ረገድ ኃላፊነቴን በሚገባ እወጣለሁ" ሲሉ ተናግረዋል። 

ለምክክሩ ስኬታማነት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን የዲመካ ከተማ ነዋሪ አቶ አርካ ዴአ በሰጡት አስተያየት "ምክክሩ መሠረታዊ በሆኑ የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ መግባባት መፍጠርን ያለመ በመሆኑ የሚጠበቅብኝን ሃላፊነት እወጣለሁ'' ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም