በትግራይ ክልል ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ ጥገና ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ ጥገና ሊካሄድ ነው
መቀሌ፤ ኅዳር 29 /2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ ጥገና በቀጣዩ ወር እንደሚጀምር የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ተወካይ አቶ አታክልቲ አርአያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመንገድ ጥገናው ስራ የሚከናወነው የኢትዮጵያ መንገዶች ፈንድ በመደበው 200 ሚሊዮን ብር በጀት ነው።
ስራው ከታኅሣሥ መግቢያ ጀምሮ ለማካሄድም ጨረታውን ያሸነፈው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መንገድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አመልክተዋል።
ኢንተርፕራይዙ የመንገድ ጥገናው እስከ ሰኔ 30ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አጠናቅቆ እንደሚያስረክብ የሚጠበቅ መሆኑን አቶ አታክልቲ አስታውቀዋል።
በክልሉ ከባድና ቀላል ጥገና ከሚደረግለት መንገድ መካከል እንዳባጉና-ዕዳጋ ህብረት፣የገንደብታ-ፈረስማይ፣የአላጀ -ቦራ፣የማይጨው -ነቅሰገ ፣ውቅሮ-ፅጌረዳ ከተሞች የሚያገናኘውን ጠቅሰዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መንገድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወላይ አሰፋ በበኩላቸው፤ ኢንተርፕራይዙ የመንገዱ ጥገና በተያዘለት ጊዜና ጥራት አጠናቆ ለማስረከብ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በሥራውም ሂደት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች ፈንድ ባለፈው የበጀት ዓመት 102 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃቱን አስታውሰዋል።
ተጠግነው ለአገልግሎት ከበቃው ውስጥ አክሱም -ዓዴት፤አክሱም-ዳዕሮ ሃፋሽና እንትጮ -ነበለት ከተሞች የሚያገናኘው መንገድን ጠቅሰዋል።