አገር በቀል የሰላም ግንባታ እሴቶችን ለማጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
አገር በቀል የሰላም ግንባታ እሴቶችን ለማጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን

አርባ ምንጭ፤ ህዳር 29 /2016 (ኢዜአ)፡- አገር በቀል የሰላም ግንባታ እሴቶችን በማጠናከር አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጋሞ ዞን ምክር ቤት አባልና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡
የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተግባር ያለመግባባት ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱና መተማመንን እንዲዳብር ለውይይት ማመቻቸት እንደሆነ ተመልክቷል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የጋሞ ዞን ምክር ቤት የሴቶችና ወጣቶች ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ዳርዛ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ ትርክቶች በህዝቡ መካከል መተማመን እንዳይኖር በማድረግ ችግር ፈጥረዋል።
የችግሩ ሰለባ የሆነው ህዝብ የመፍትሄው አካል መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ምክር ቤቱ በየደረጃው የሚገኙ አባላትን በማስተባበር ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ መሳካት የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።
በየአካባቢያችን ሰላምን የምንገነባበትና ገዥ የሆነ ዕሴት አለን የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ እነዚህን ሀብቶች በመጠቀም አገራዊ ሰላምና አንድነት ግንባታን ለማጠናከር እያመቻቸ ላለው የምክክር ኮሚሽን ስኬታማነት የሚጠበቅብንን እንወጣለን ሲሉ ብለዋል።
ከጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ መንግስቱ ደምሴ በበኩላቸው ፤ የአገር ልማትና ብልጽግና ለማምጣት ከሁሉ በፊት አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
እንደአገር በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩና ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን አሳታፊ በሆነ መልኩ የሚፈታበት ዕድል አለመፈጠሩ ችግሮቹ እየተንከባለሉ መምጣታቸውን አውስተዋል።
በዚህም ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤና ዕውቀት እንዲሁም ግንኙነት የሌለው ትውልድ ጭምር ሰለባ እንዲሆን እንዳደረገው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ይህንን የቆየ ችግር መፍታት የሚያስችል እድል በመሆኑ ሃገር በቀል እሴቶችን በመጠቀም መፍታት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
በጋሞ ባህልና ወግ ችግሮችን ያለምንም ቀሪ ቂምና ቁርሾ በዘላቂነት የሚፈቱበት " በዱቡሻ" የተሰኘ ባህላዊ የሸንጎ ስርዓት መኖሩን ጠቁመው፤ ይህንን ነባር ባህል ተጠቅመን አለመግባባቶችን በመፍታት ለኮሚሽኑ ስራ ስኬታማነት እንሰራለን ብለዋል።
የሀሳብ ልዩነቶችን በመቻቻልና በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ በመግባባት መፍታት ለሀገር በጎ ገጽታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።
አቶ መንግስቱ አክለውም ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለመጪው ትውልድ ጠንካራ አንድነት ያላትና የበለጸገች አገር ማውረስ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ስልጣኔ በተስፋፋበት ዘመን ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመምከር መፍታት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ተፈራ ኦይቻ ናቸው።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራ የህዝቡ የዘመናት ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና እፎይታን የሚሰጥ ፤ ለዚህም መሰካት ሁሉም በየደረጃው ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ደግሞ ሌላ አዲስ አማራጭ ሳይሆን የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን ባህልና ወግ እንዲሁም ልምድ መሰረት በመፈተሽ ዘመናት ያስቆጠሩ ችግሮችን ጭምር በማውጣት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እንሰራለን ነው ያሉት።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳመለከቱት፤አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ስራ ውጤታማ የሚሆነው ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሲወጣ ነው፤ በዚህ ረገድ ሁሉም ለንግግርና ሰላም ግንባታ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ በቂ ግንዛቤ መስጠት ያስፈልጋል፡፡