ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 627 ተማሪዎችን አስመረቀ።

ዩኒቨርስቲው በፓይለት፣ በማርኬቲንግ፣ ኤርክራፍት ሜንቴናንስና በሌሎች የሙያ መስኮች  ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ከአፍሪካ አገራት የመጡ ናቸው።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤  አየር መንገዱ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ የራሱን የሰው ሀይል በራሱ ማስተማርና ማብቃት የሚችል ትልቅ ድርጅት ነው።

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ውድድሩ ከአፍሪካ ጋር ሳይሆን ከፍተኛ ሀብት ካላቸውና በቴክኖሎጂ ከዘመኑ አየር መንገዶች ጋር መሆኑን ተናግረው፤ ተወዳድሮ በትርፋማነትና በእድገት የቀጠለ ድርጅት ነውም ሲሉም አክለዋል።


 

ለአየር መንገዱ እዚህ ላይ ለመድረሱ በተለያየ ጊዜ ተቋሙን የመሩት ሰዎች  በነበራቸው ራዕይ፣ ዕውቀትና ሰራተኞች በታታሪነትና በቁርጠኝነት ማገልገላቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎችም በቁርጠኝነትና በጥንካሬ በመስራት የድርጅቱን እድገት ለማስቀጠል ሀላፊነት መውሰድ  እንዳለባቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ካሴ ይማም በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን የስልጠና አይነት በማስፋት ለአቬየሽን ዘርፍ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም