የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማረጋገጥ ብዝኃነትን እንደ ትልቅ አቅምና ኃብት መጠቀም ይገባናል - የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማረጋገጥ ብዝኃነትን እንደ ትልቅ አቅምና ኃብት መጠቀም ይገባናል - የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማረጋገጥ ብዝኃነትን እንደ ትልቅ አቅምና ኃብት መጠቀም ይገባናል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
የዘንድሮ 18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የማጠቃለያ መርኃ ግብር "ብዝኃነትና እኩልነት፥ ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ኃሳብ የኢትዮጵያ ቀን በጅግጅጋ ከተማ ስታዲየም በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል ቡድኖች ታድመዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ብዝኃነት በጋራ መሥራት፣ በጋራ መልማትና ማደግ እንዲሁም ውበት ነው።
ብዝሃነት በአግባቡ ከተጠቀምንበት አቅምና ኃብት ነውም ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት።
ብዝኃነታችን በአንድነታችንና በእኩልነታችን ላይ መሰናክል እንዳይሆን በጋራ መሥራትና ሰላማችንን በጋራ ማረጋገጥ ይገባናል ብለዋል።
ዛሬ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንሄደው አባቶቻችን ባቆዩልን ነጻነት ነው ሲሉም ፕሬዚደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አክለዋል።
የአሁኑ ትውልድም ሃላፊነቱን የሚወጣው አባቶቹ ያቆዩለትን ነጻነት ጠብቆ ሰላሟ የተጠበቀ አገር ለመጪው ትውልድ ማውረስ ሲችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለሁሉም የምትበቃ አገር መሆኗን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቷ የጋራ ችግራችንን በጋራ ፈትተን የሀገራችንን ታላቅነት ማረጋገጥ ይገባናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አንድነታችንን የምናጠናክርበት በመሆኑ የአንድ ቀን በዓል ብቻ ሳይሆን የሁል ጊዜ ሥራችን ሊሆን ይገባል ብለዋል።