ቀጥታ፡

መንግስት ለሦስተኛ ጊዜ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ድጋፍ ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዕርዳታ መመደቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2016(ኢዜአ)፦በ2016 በጀት ዓመት መንግስት ለሦስተኛ ጊዜ አጋር አካላትን  በማስተባበር የቅድሚያ ቅድሚያ  ድጋፍ ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዕርዳታ መመደቡን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በአጋር አካላት ይቀርብ የነበረው ዕርዳታ በጊዜያዊነት መቋረጡን ተከትሎ በዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ይደርስ የነበረውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ መንግስት የራሱን እርምጃ ወስዷል።

በዚህም መሰረት በሁለት ተከታታይ ዙሮች ብር 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የአይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ወገኖች ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም አስከ ህዳር ወር 2016 ዓ.ም ባሉት አምስት ወራት ውስጥ ተደራሽ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለሦስተኛ ዙር በቅርቡ ወደ ስራ የተመለሱትን አጋር ድርጅቶች ጭምር በማስተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው ፍላጎት ውስጥ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ድጋፍ ለሚፈልጉ የተፈናቀሉ ዜጎችና በድርቅ አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።

በዚህ መሰረትም ከ 867 ሺ ኩንታል በላይ የምግብ ዕርዳታ በአይነት እንዲሁም ከብር 560 ሚሊዮን በላይ ጥሬ ገንዘብ፤ በታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም ለማሰራጨት ሥራውን አጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

ዕርዳታ የማጓጓዙ ሥራም ከህዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን ገልጾ አጠቃላይ ድጋፉም በገንዘብ ሲሰላ ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን መግለጫው ያሳያል።

በቅርቡ በድርቅ አደጋ የተጠቁ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸውም ተጠቁሟል ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም