በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋጥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋጥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።
18ኛ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የማጠቃለያ መርሃ-ግብር "ብዝኃነትና እኩልነት፥ ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በማጠቃለያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የባህል ቡድኖች በጅግጅጋ ስታዲየም ባህላዊ ትርኢት አቅርበዋል።
በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል ቡድኖች ታድመዋል።
በዚሁ ወቅት የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ኢትዮጵያውያን ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ብዙ በመሆናቸው ያሉንን መልካም እሴቶች በማጠናከር ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ መስራት ይገባናል ብለዋል።
በዜግነት ድርና ማግ የተሳሰርን በመሆናችን አንድነታችንን ለሚያጸኑ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተን ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ማጽናት ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለዚህም የአብሮነታችንን እሴቶች በማጠናከር ዘመኑን የሚመጥን የጋራ አስተሳሰብ ማጎልበት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዓሉ መከበሩ ኢትዮጵያውያን አንዱ የሌላውን ገጽታና ውበት እንድንመለከትና ውበታችንን በሚገባ እንድናይ ያስቻለ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በብዝሃነት ውስጥ ያለ ውበት የሚታይበትና ህብረ-ብሄራዊ አንድነት የሚጸናበት ዕለት መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህንን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን በማጠናከር ከችግርና ከአረንቋ ለመውጣት እጅ ለእጅ ተያይዘን በትብብር መስራት ይገባናል ሲሉም አክለዋል።
ከዚህ ቀደም አጋር በሚል ስያሜ በገዛ አገራቸው የመወሰን መብት ተነፍገው የዳር ተመልካች የነበሩ አካላት ዛሬ ላይ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ልማትና አስተዳደር እንዲሳተፉና እንዲወስኑ የተመቻቸውን እድል በመጠቀም የኢትዮጵያን ብልጽግና የማፋጠን ስራ ላይ ትኩረት ልታደርጉ ይገባል ብለዋል።
የ18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ከህዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዚህም መሰረት ኅዳር 25፣ 26፣ 27 እና 28 በቅደም ተከተል የወንድማማችነት፣ የብዝኃነት፣ የአብሮነትና የመደመር ቀን በሚል ተሰይመው በተለያዩ ሁነቶች ተከብረዋል።
የበዓሉ ማጠቃለያ ሥነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት በጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ መርሀ ግብሮች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።