የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ የአብሮነት እሴትን ያጠናክራል - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ የአብሮነት እሴትን ያጠናክራል - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ ዜጎች ለረዥም ዘመን ያቆዩትን የአብሮነት እሴት ይበልጥ እያጠናከረው መምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
የ18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የማጠቃለያ መርኃ-ግብር "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ኃሳብ በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል ቡድኖች ታድመዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የበዓሉ መከበር ከልዩነት ይልቅ አብሮነትን ለማጠናከር ሰፊ እድል እየፈጠረ ነው ብለዋል።
በተለይም ከለውጡ ወዲህ ባሉ ዓመታት የተከበሩት በዓላት፣ ከመራራቅ ይልቅ አብሮነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጥርጣሬ ይልቅ መተማመንን እየፈጠሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የዘንድሮ በዓል ኢትዮጵያውያን ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት አገራዊ ምክክር ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ዋዜማ መከበሩ ልዩ ትርጉም እንዲሰጠው ያደርጋል ብለዋል።
ብዝኃነት ሕብረ ብሔራዊ ማንነት ነው፤ ብዝኃነት በልዩነት ውስጥ ያለ አገራዊ አንድነት ነው፣ ብዝኃነት ብርታት የጥምረትና የሰጥቶ መቀበል ውጤት ነው ሲልም ተናግረዋል።
በመሆኑም በብዝኃ ማንነት ላይ የተገነባውን አገራዊ አንድነት እንዳይሸረሸር በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ማጠናከር ይገባናል ብለዋል።
ችግሮች ሲያጋጥሙ በመመካከርና በመግባባት መፍትሔ መስጠት እንደሚገባም ነው አቶ አገኘሁ ተሻገር የገለጹት።
ሕዝቦች በተለያዩ ጊዜያት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ችግሮችን በጉልበት ለመፍታት የሚደረጉ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች ተገቢ አለመሆናቸውንም በንግግራቸው አንስተዋል።
የብዝኃነት፣ የእኩልነትና የአንድነት መስተጋብራችንን በማጎልበት የአገረ መንግሥት ግንባታውን በዘላቂነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ነው ያመለከቱት።
ለዚህም የተጀመረውን የተቋማት ግንባታ ማፋጠን እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።