በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስህብ ስፍራዎችን ለማልማት እየተስራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስህብ ስፍራዎችን ለማልማት እየተስራ ነው
ሚዛን አማን ፤ ኅዳር 29 ቀን 2016 (ኢዜአ) ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የመስህብ ስፍራዎችን ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህል ፣ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ ።
ክልሉ በቱሪዝም ሀብት የታደለ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳልተቻለ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አክሊሉ ለማ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የክልሉ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እና ሰው ሰራሽ መስህቦች መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ ለጎብኚዎች ምቹ እንዳይሆኑ አድርጓል።
ቢሮው ችግሩን ለማቃለል በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ማነቆ ለመፍታት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱን አውስተዋል።
በተለይ በካፋ ዞን ከቦንጋ ከተማ የቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የ"እግዜር ድልድይ "እና በሸካ ዞን ውስጥ ያለውን የ"ጋንዶች ሀይቅ" ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የመንገድ ግንባታ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን የክልሉን ባለሀብቶች በማሳተፍ ጭምር በማልማት ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ ለማሳደግ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በፌዴራል መንግሥት በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ እየለሙ ያሉ የኮይሻ እና ደንቢ ፕሮጀክቶችም ሲጠናቀቁ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያስገኙም ጠቁመዋል።
በክልሉ ያሉት ሁለት ብሔራዊ ፓርኮች፣ ባህላዊና ጥንታዊ ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
አነዚህን መስህቦች በተለያዩ አማራጮች የማስተዋወቅ ስራም ልዩ ትኩረት እንደተሰጠም አብራርተዋል።
የቱሪስት ገቢ ማሰባሰቢያ ደንብ የማዘጋጀቱ ተግባር እየተጠናቀቀ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አክሊሉ፤ በክልሉ ውስጥ አስጎብኚ ማኅበራት እንዲደራጁ የአሠራር መዋቅር የመዘርጋት ሂደት እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ የካፋ ዞን ነዋሪ አቶ አሰፋ ገብረማርያም በሰጡት አስተያየት ፤ በአካባቢው የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች በአግባቡ ቢለሙ ከክልሉ አልፎው ለሀገር የሚተርፉ እምቅ አቅም እንዳለ ተናግረዋል።
በተለይ የመስህብ ስፍራዎቹን የአካባቢው ህዝብ በባህላዊ ሥርዓት ጠብቆ ያቆያቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህን ማዘመንና ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የተፈጥሮ መስህቦች ተጠብቀው እንዲቆዩ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ የማልማት ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ በክልሉ የኮንታ ዞን ነዋሪ አቶ በላይነህ ዶጮ ናቸው።
በአካባቢያቸው ያሉት የጨበራ ጩርጩራ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።