ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከ17 ሀገራት ጋር የአየር ትራንስፓርት አገልግሎትን ለመጀመር እና ለማስፋፋት ተስማማች

አዲስ አበባ፤ህዳር 29/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከ17 ሀገራት ጋር የአየር ትራንስፓርት አገልግሎትን ለመጀመር እና ለማስፋፋት ስምምነት አድርጋለች።

ስምምነቱ የተፈጸመው ከ17 የአፍሪካ፣ የሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር መሆኑም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዮዬሽን ባለስልጣን እና በሀገራቱ አቻ ተቋማት መካከል ስምምነቱ የተፈረመው በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ በተካሄደው አመታዊ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርድር ጉባኤ ላይ ነው።

በዚህም መሰረት ከናይጄሪያ፣ ጋና፣ ሞሮኮ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሴራሊዮን እና ዙምባብዌ ጋር ያለገደብ የአውሮፕላኖችን ምልልሶች ለማከናወን፣ የአየር መንገዶችን ውክልና ለማስፋት፣ የትራፊክ መብቶችን ለመስጠትና ተጨማሪ መዳረሻ ቦታዎችን ያለገደብ ለመፍቀድ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ስምምነት ተፈርሟል።


 

ከታንዛኒያ፣ ከሲሺልስ እና ጋቦን ጋር ደግሞ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ አየር መንገዶች በሀገራቱ ተጨማሪ የበረራ ምልልስ ማድረግ የሚያስችላቸው ስምምነት ተደርጓል።

ሌላው የኢትዮጵያን ሲቪል አቭዬሽን ስምምነት ያደረገው ከራሽያ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ፖላንድ፣ ፊንላንድ፣ ኩዌት፣ ፓኪስታን፣ ባንግላንዲሽ እና ሱሪናም ጋር ሲሆን ፤ ስምምነቱ የበረራ የምልልስን በመፍቀድ የገበያ እድሎችን ለማስፋት የሚያስችል ነው።


 

እነዚህ ስምምነቶች ኢትዮጵያ ከአቪዬሽን ኢንዱስትሪው እያገኘች ያለውን ጥቅም የሚያሳድግ እንደሆነም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሳኡዲ አረቢያ በተደረገው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርድር ዓለም አቀፍ ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ 97 ሃገራት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም