የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የዋዜማ ሥነ-ስርዓት እየተካሄደ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የዋዜማ ሥነ-ስርዓት እየተካሄደ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ዋዜማ ሥነ-ስርዓት በሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ እየተካሄደ ይገኛል።
በዝግጅቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል ቡድኖች ታድመዋል።
በሥነ-ስርዓቱም የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል ቡድን ተወካዮች አንድነታቸውን፣ አብሮነታቸውንና ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያንጸባርቁና የባህል የልምድ ልውውጥ ዝግጅቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
በነገው ዕለት በጅግጅጋ ከተማ በሚኖረው ዝግጅትም የዘንድሮው 18ኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን በዓል የማጠቃለያ ሥነ-ስርዓት የሚካሄድ ይሆናል።
ባለፉት የኅዳር-25፣ 26 እና 27 ቀናት በቅደም ተከተል የወንድማማችነት፣ የብዝኃነትና የአብሮነት ቀናት በድምቀት የተከበሩ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት በነበረው የኅዳር 28 "የመደመር ቀን" በማስመልከት የምክክር መድረክ እና የጎዳና ላይ የባህል ትርዒት ተካሂዷል።
በመድረኩም "የመግባባት ዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳባዊ ዳራ እና ኢትዮጵያዊ እሳቤ" እንዲሁም "የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትና የሶማሌ ክልል ሕዝብ ተጠቃሚነት ከለውጡ በፊትና በኋላ" የሚሉት የመነሻ ጽሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
የ18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ከህዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት እየተከበረ መሆኑ ይታወቃል።