የመደመር ቀን አካል የሆነው የአደባባይ የባህል ትርዒት በጅግጅጋ ጎዳናዎች ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር ቀን አካል የሆነው የአደባባይ የባህል ትርዒት በጅግጅጋ ጎዳናዎች ተካሄደ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 28/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክብረ በዓልን በማስመልከት የመደመር ቀን የአደባባይ የባህል ትርዒት በጅግጅጋ ከተማ ጎዳናዎች ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "የመደመር ቀን" አካል በሆነው የባህል ትርዒት ከአራቱም ማዕዘናት ጅግጅጋ የከተሙ የባህል ቡድኖች የ3 ኪሎ ሜትር የአደባባይ የባህል ትርዒት በጅግጅጋ ከተማ ጎዳናዎች አሳይተዋል።
ቀደም ብሎም "የመደመር ቀን"ን ታሳቢ በማድረግ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የምክክር መድረክ መካሄዱ ይታወሳል።
የ18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ከህዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ መርኃ ግብሮች በድምቀት መከበሩን ቀጥሏል።
በዚህም ኅዳር-25፣ 26 እና 27 በቅደም ተከተል የወንድማማችነት፣ የብዝኃነትና የአብሮነት ቀናት በድምቀት የተከበሩ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት በተከበረው ኅዳር-28 ደግሞ "የመደመር ቀን" አስመልክቶ የባህል ቡድኖች ደማቅ የጎዳና ላይ የባህል ትርዒት በማሳየት ነው።
በነገው ዕለትም 18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በኅዳር-29 2016 ዓ.ም "የኢትዮጵያ ቀን" በጅግጅጋ ከተማ የማጠቃለያ መርኃ ግብር እንደሚደረግ ይጠበቃል።