ቀጥታ፡

ማዕከሉ አፍሪካውያን ባህልና ስልጣኔያቸውን ለነገው ትውልድ እንዲዘክሩ የሚያደርግ የዚህ ትውልድ ትልቅ አሻራ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 28/2016(ኢዜአ) ፦የዓለም ጥቁሮች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል  አፍሪካውያን ባህልና ስልጣኔያቸውን ለነገ ትውልድ እንዲዘክሩ የልህቀት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል የዚህ ትውልድ ትልቅ አሻራ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የዓለም ጥቁር ህዝቦች የታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል ዋና ፅህፈት ቤቱን ዛሬ በአዲስ አበባ ከፍቷል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ማዕከሉ ለጥቁር ሕዝብ ታሪክና ቅርስ መሰረት የሚጥል፣ ማህበረሰብ አቀፍ የባህል ልማት ለማምጣትና ለአፍሪካ ወጣቶች አንድነትና ትብብርን ለማጎልበት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የጥቁሮች ታሪክ፣ ባህልና ስልጣኔያቸውን ለነገ ትውልድ እንዲዘክሩ ዕድል የሚፈጥር ብሎም የትምህርትና ቅርስ ጥናት የልህቀት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል የዚህ ትውልድ ትልቅ አሻራ እንደሆነም ገልጸዋል።

ማዕከሉ ነጻነት የሚዘክርና ባህልን ለማሳደግ እንዲሁም መጪውን ትውልድ  በእውቀት ለመቅረጽ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

የማዕከሉ በኢትዮጵያ መከፈት፤ ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝብ ነጻነት ለከፈለችው መስዋዕትነት ዋጋ የሚሰጥና ወደፊትም የመሪነት ሚናዋን እንድትወጣ ትልቅ ኃላፊነት የሚያላብስ መሆኑን አመልክተዋል። 

ኢትዮጵያ ማዕከሉን ለመደገፍ ታሪካዊና ነባር ሚናዋን እንደምትወጣም ነው የተናገሩት።

የማዕከሉ ዕውን መሆን ለመጭው ትውልድ ታሪክን ለማውረስ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አፍሪካዊ ዳያስፖራን ጨምሮ ሁሉም ለማዕከሉ ድጋፍ በማድረግ  ታሪካዊ ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል።  


 

የወቅቱ ትውልድ የአባቶችን አደራ ጠብቆ ማዕከሉን መደገፍ አለበት ነው ያሉት። 

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የጤና፣ ሰብአዊ ጉዳዮችና ማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፤  ማዕከሉ የወደፊት የጥቁር ማህበረሰብ ተስፋና ቃል ኪዳን እንዲሁም የትናንት መዘከሪያ ቅርስ ነው ብለዋል። 

ጥቁሮች ለዓለም ከፍተኛ አበርክቶ ቢኖራቸውም ታሪካቸው ሳይዘከር መቆየቱን ይልቁንም ተዛብቶ እንደቀረበ አስታውሰዋል። 

ማዕከሉ ይህን የተዛባ የጥቁሮች ትርክት መለወጥና ትክክለኛውን ታሪክ በራሳችን ለመተረክ አቅም የሚሆን፣ የጋራ ታሪክ ለመሰነድ፣ የባህል ልውውጥ እና ፈጠራን ለማጎልበት ያስችላል ብለዋል።

በአፍሪካ ሕብረት በ2063 አጀንዳ እንዲሁም በሕብረቱ ቻርተር የአፍሪካ ባህል ሕዳሴን ማረጋገጥ አንዱ ፕሮጀክት በመሆኑ ይህ ማዕከል በአዲስ አበባ መከፈቱ በአፍሪካ ቻርተር የሚደገፍ  ነው ብለዋል። 

የባህል ልውውጥና ፈጠራ ለማጎልበት፣ ድምጽን ለማሰማት፣ ብዝሃነትና የቅርስ አሻራዎች መዘከሪያ እንዲሁም የጥቁር ሕዝብ ክብርና ከፍታ የሚሰጥ ወሳኝ ተቋም እንደሚሆንም ነው አምባሳደሯ የገለጹት።

የማዕከሉ መስራች አባል ሮቢን ዎከር እንዳሉት፤ ማዕከሉ የምዕራባውያንን የተዛባ የጥቁሮችን ትርክት ማስተካከል፣ ስልጣኔ ለመዘከር፣ ሐቀኛ ታሪክ ለመሰነድና ለትውልዱ ለማስተላለፍ እንደሚበጅ ገልጸዋል።

በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች የሚጋሯቸውና የተወራረሷቸው ባህል፣ ጥበብና ቅርሶች እንዳሏቸው ገልጸዋል።

ይህን ማሳወቅና የተዘረፉ ቅርሶችን በማስመለስ በአንድ ማዕከል ለዕይታ እንዲዘከሩ የማድረግ እንዲሁም ለመላው ጥቁሮች አንድነትና ትስስር ማጎልበት እንደሚበጅ ገልጸዋል።

የማዕከሉ ዓለም አቀፍ ሊቀመንበር ጸጋዬ ጨማ በበኩላቸው ማዕከሉ ለመመስረት የረጅም ጊዜ ጥረት መደረጉንና  መስራች አባላቱ በተናጥል ብርቱ ጥረት ስለማድረጋቸው አንስተዋል። 

በቀጣይም መላው የአፍሪካ ዳያስፖራና የተቋማትን ድጋፍ በማስተባበር ማዕከሉ በአዲስ አበባ የሚያስገነባውን ሙዚየም ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን ዕውን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ማዕከሉን ዕውን ማድረግ የተቻለው በለንደን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስትና በአፍሪካ ሕብረት ትብብር መሆኑን ገልጸው፣ ማዕከሉ ከዚህ ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም