ቀጥታ፡

የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 28/2016 (ኢዜአ) ፦ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የጃፓን ኩባንያዎችና ባለኃብቶች የሚሳተፉበት የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በፎረሙ በጃፓን የኢትዮጵያ ሚሲዮን በኩል የተመለመሉ የጃፓን ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

ለቢዝነስ ልዑካኑ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት እድሎችና ማበረታቻዎች እንዲሁም ሕጎችን በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል።

በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያና ፓሲፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ካላቸው አገራት አንዷ ነች።

በዚህ ረገድ የጃፓን ኩባንያዎች ልምድና እውቀት ለአገሪቱ ቀጣይ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ስላላቸው ትልቅ ቦታ እንሰጣለን ሲሉ ተናግረዋል።

የቢዝነስ ፎረሙ በሁለቱ አገራት መካከል በኮቪድ-19 እና በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያና ጃፓን የረጅም ጊዜ የንግድ ትስስር ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቅሰው በተለይም የኢትዮጵያ ቡና በከፍተኛ ደረጃ ተደራሽ ከሚሆንባቸው አገራት ዋነኛዋ እንደሆነች ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የቅባት እህሎች ወደ ጃፓን እንደምትልክ ገልጸው ከጃፓን ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የፋብሪካ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡም ነው ያመላከቱት።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለቱ አገራት መካከል አዳዲስ ገበያዎችን በመፍጠር በአገራቱ መካከል ያለውን የንግድ መጠን ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም