ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት --ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል

ደሴ ፤ህዳር 28/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ጠንካራና  ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ እና ሰላሟን ዘላቂ  ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት  የምስራቅ አማራ ኮማድ ፖስት ሰብሳቢና የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል ገለጹ፡፡

በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምስራቅ ዕዝ 18ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ቀን በዓል "ብዝሀነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በኮምቦልቻ ከተማ አክብሯል፡፡


 

ሌተናል ጄነራል አሰፋ ቸኮል በወቅቱ እንደገለጹት፤ የህዝብን ደህንነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሰራዊቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ነው፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሲከበር የኢትዮጵያ አንድነት፣ ልማትና ሰላም በሚያጠናክር መልኩ እንደሆነ ተናግረዋል።

"የጥንት አባቶችን ባህልና እሴት ጠብቀን የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም የበለጠ እናፀናለን" ያሉት ሌተናል ጄነራሉ፤ ህብረተሰቡም ደጀንነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በየአካባቢው የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጠል ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል።

በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምስራቅ ዕዝ አባል ኮሎኔል ዘሪሁን ሽፈራው በበኩላቸው፤ ሰራዊቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልጅ በመሆኑ የሕዝብንና የአገርን ሰላም በማረጋገጥ የተጣለበትን ሃላፊነት በሚገባ እንደሚወጣ ገልጸዋል።

ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ልንመክርና " አጥፊን ተው ልንል ይገባል'' ያሉት ደግሞ በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉት መጋቢ ስርዓት ቀሲስ ወንድዬ ማስረሻ ናቸው፡፡

የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ መሃመድ አሊ በበኩላቸው፤ "ባህልና እሴቶቻችንን ጠብቀንና የጥንት ማንነታችን ተገንዝበን የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና ማፋጠን አለብን" ብለዋል፡፡

በበዓሉ ላይ  የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኮምቦልቻ ከተማና የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች፤ ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም