ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን የጎላ አስተዋፅኦ አጠናክራ ትቀጥላለች - ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 28/2016 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮ ያላትን የጎላ አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ የሰላም ማስከበር ማዕከል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ተናገሩ።

የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አጋርነትን በተመለከተ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ካደረጉ ከተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች ጋር ተወያይቷል።


 

የመከላከያ የሰላም ማስከበር ማዕከል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዓለም የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አርአያ የሚሆኑ ተግባራትን አከናውናለች።

ከዚህ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መከላከያ በጠንካራ ሪፎርም የተደገፈ ዘመኑን የሚመጥን ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ እየተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰላም ማስከበር ሥራ ኢትዮጵያ ያላትን የካበተ ልምድ ከሌሎች አካላት አቅም ጋር በመደመር የበለጠ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሰላም ማስከበሩ ሥራ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት አጋርነት በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

ማዕከሉ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ አጋዥ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሥልጠናና ትምህርት ዲን አቶ ከድር አባቡልጉ ናቸው።

ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ መሳካት የሚደረገው አስተዋጽዖ ለማጠናከር የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

አጋር አካላት ኢንስቲትዩቱን በፋይናንስ፣ በቴክኒክና የተለያዩ ልምዶችን በማካፈል እያገዙ እንደሚገኙ ገልጸው ይህ ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም