የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር ለስፖርት ማጠናከሪያ የሚውል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር ለስፖርት ማጠናከሪያ የሚውል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ባህር ዳር፤ ህዳር 28/2016 (ኢዜአ) ፦ የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር ለስፖርት እንቅስቃሴ ማጠናከሪያ ድጋፍ የሚውል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የውል ስምምነት ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ስፖርት መምሪያ ጋር ተፈራረመ።
በአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የሰሜን ቀጠና ጽህፈት ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ እሸቴ የማታ ዛሬ በተካሄደው የፊርማ ስነ-ስርዓት ወቅት እንዳሉት፤ባንኩ ከሚሰጠው የባንክ አገልግሎት ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
ባንኩ ባለፈው ዓመት የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብን ለማጠናከርና ‘‘አማራ ባንክ ጣና ዋንጫ’’ በሚል በባህር ዳር ለተካሄደው የቤትኪንግ ፕሪሜርሊግ የእግር ኳስ ውድድር 8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ዛሬ የተፈራረሙት የውል ስምምነት ደግሞ ባንኩ በባህር ዳር ከተማ በሶስት ቦታዎች ለሚካሄድ ነፃ የማህበረሰብ አቀፍ የጤናና የአካል ብቃት ስፖርት እንቅስቃሴ ስልጠና የሚውል የ540 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
በቀጣይም ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር በጎንደር፣ በደሴና ደብረማርቆስ ከተሞች ለሚካሄድ ነፃ የማህበረሰብ አቀፍ የጤናና የአካልብቃት እንቅስቃሴ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አሰፋ በበኩላቸው፤ ባንኩ ዛሬ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት እንቅስቃሴ እንዲነቃቃና ህብረተሰቡ ጤንነቱን እንዲጠብቅ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ባንኩ ባለፈው ዓመት በባህር ዳር ከተማ ለተካሄደ የቤትኪንግ ፒሪሜርሊግ ተሳታፊ የእግር ኳስ ውድድር ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አውስተዋል።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ለአንድ ዓመት ነፃ የማህበረሰብ አቀፍ የጤናና የአካል ብቃት ለሚሰጡ አሰልጣኞች የላብ መተኪያ እንደሚውል ተመልክቷ
በዚህም በሳምንት ሶስት ቀን በከተማዋ በባለእግዚአብሄር፣ አዝዋና አባይ ማዶ ከጥዋቱ 12 ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት በሚካሄደው ነፃ የማህበረሰብ አቀፍ የጤናና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል።
ይህም ባህር ዳርን የስፖርት ቱሪዝም ከተማ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካትና ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ህብረተሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ላለው ጥረት ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አብራርተዋል።
የአማራ ባንክ በስፖርቱ ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ድጋፍም ሌሎች ባንኮች ተግባሩን በአርዓያነት ወስደው እንዲደግፉ አቶ አብርሃም ጥሪ አቅርበዋል።