በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በሰሜን ሸዋ ዞን የእንሳሮ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በሰሜን ሸዋ ዞን የእንሳሮ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
ደብረ ብርሃን ፤ ህዳር 28/2016 (ኢዜአ) ፦ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው የህግ ማስከበር ስራ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆነው በማገዝ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በሰሜን ሸዋ ዞን የእንሳሮ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ።
በእንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ በወቅታዊ የፀጥታና ሰላም ማስክበር ዙሪያ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
የከተማው ነዋሪ በኩረ ትጉሀን አባ ሀረገወይን አድማሱ እንደገለፁት፤ በአካባቢው እየተስተዋለ ያለው የሰላም መታጣት ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል።
ለዚህም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ወጣቶችን በመምከር ሚናቸውን በመወጣት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በአካባቢው የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የአካባቢውን ህዝብ በስራ በመደገፍ የህዝብ ደጀንነቱን እያረጋገጠ ነውብለዋል።
ሰላምን በዘላቂነት ማረጋጋጥ የሚቻለው በትብብርና በመነጋገር በመስራት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለዚህም የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
ባለፉት ወራት በአካባቢው በደረሰው የሰላም መታጣት በኢኮኖሚም ሆነ በማህበራዊ እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ማሳደሩን የገለፁት ደግሞ አቶ ግዛቸው ታምራት ናቸው።
አሁን ላይ የሰላም መታጣት ችግሩ መሻሻሉን ጠቅሰው፤ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ ሁሉም በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መከላከያ ሰራዊትም ልጆቻችን እና የአገር ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቁ በመሆናቸው ልናከብራቸውና ልናግዛቸው ይገባል ብለዋል።
የሰላም እጦት የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴትን የሚያናጋ በመሆኑ በጋራ በማውገዝ ለጠንካራ አገር ግንባታ በትብብር መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጌታቸው ሸንቁጤ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አልምቶ ለመጠቀም ሰላም አስፈላጊ ነው።
በመንግስት እና ባለሀብቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በሰላም እጦት ሊደናቀፉ እንደማይገባ አመልክተው፤ "ለዘላቂ ሰላም ግንባታም አብረን እንሰራለን'' ብለዋል።
የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባል እና የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በወቅቱ እንደገለፁት፤ ባለፉት ጊዜያት በተካሄደው የተቀናጀ የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ የአካባቢውን ሰላም ወደ ተሻለ ሁኔታ ማምጣት ተችሏል።
አሁንም ሰላም ወዳዱን ህዝብ በማስተባበር የተገኘውን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ተደራጅቶ ሰላም የማስክበሩን ስራ ማከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች በሰላም ችግር እንዳይደናቀፉ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና መላው የአካባቢው ነዋሪ ሰላም ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎችን በማገዝ የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመከላከያ ሰራዊት የ101ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር የኦፕሬሽናል ምክትል አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ማቲያስ ማንዴቦ በበኩላቸው የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ሰራዊቱ ህብረተሰቡን በማስተባበር ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እየደገፉ መሆኑን ገልፀዋል።
በውይይት መድረኩ የሀይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ በየደረጃው ያሉ አመራር አባላትና የፀጥታ ሃይሎች ተሳታፊ ሆነዋል።