ኢትዮ-ቴሌኮም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ዲጂታል መሠረተ ልማትን ማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 28/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮ-ቴሌኮም ከኦሮሚያ ክልል ጋር የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምኑና የስማርት ሲቲ ትግበራን እውን የሚያደርጉ ዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ በምክትል ፕሬዚደንት ማዕረግ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ መስከረም ደበበና የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ ፈርመውታል።


 

የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ መስከረም ደበበ በዚህ ወቅት ክልሉ የማህበራዊና ተቋማዊ አገልግሎቶችን በስፋት የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም የትምህርት፣ የጤና፣ የቱሪዝምና መሠል አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ይገኛል።

ለዚህም ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ አሰራሮችን በማስረጽ ምርትና ምርታማነትን ማጎልበት ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነም አብራርተዋል።

ስምምነቱ በዋናነት በክልሉ ያሉ ዞኖችን፣ ወረዳዎችንና ከተሞችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የሚፈለገው የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

በዋናነት የንግድ ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋት ላይም እንዲሁ የተደረገው ስምምነት ወሳኝ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ስምምነቱ የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለማጎልበትና ከማህበረሰቡ ለሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው ተብሎ ታምኖበታል።


 

የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሞችን የማዘመን ስራ እየተለመደ መጥቷል።

የሸገር ከተማ ምስረታ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር የተደረገው ስምምነት ከተማዋን ይበልጥ ለማዘመን ይረዳል ብለዋል።

በተለይም በቴክኖሎጂ የበለጸገች፣ ተስማሚና አምራች ከተማን ለመፍጠር የስምምነቱ ሚና ጉልህ እንደሚሆንም አንስተዋል።


 

ተቋሙ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የተቋማትን የዲጂታል አገልግሎቶች ማስፋት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ናቸው።

ይህም ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።

ዛሬ የተፈረሙት ስምምነቶች በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በማፋጠን ዘመናዊነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በዋናነት ዲጂታላይዝ ተቋማትን መፍጠር፣ የትምህርት ተደራሽነት፣ የማዕድን ሃብት ልየታና ምርት ማዘመን እንዲሁም የግብርና ስራን በቴክኖሎጂ መደገፍ ዋነኞቹ ናቸው።

በተጨማሪም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎቶች፣ የጤና፣ የመሬት አስተዳደርና የስማርት ሲቲ ግንባታንም እንዲሁ በቴክኖሎጂ ማዘመን የስምምነቱ አካል ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ስምምነቱ የክልሉን ሃብት በተገቢው ጥቅም ላይ ለማዋል በእጅጉ የሚያግዝና የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያቃልል መሆኑን ጠቁመዋል።

ስራውን በሚፈለገው መልኩ ለማከናወን ኢትዮ-ቴሌኮም በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም