የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጓል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጓል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 28/2016 (ኢዜአ)፦ የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያን ጨምሮ ሌሎች ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርኃ ግብር ዓመታዊ የልማት ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ የኢንዱስትሪ ልማት የኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በአስር ዓመት የልማት ዕቅድና በአገር በቀል የምጣኔ ኃብት ሪፎርም አጀንዳ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
ይህንንም ተከትሎ የዘርፉን ውጤታማነት የሚያጠናክሩ የመሰረተ ልማትና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
ጎን ለጎንም የዘርፉን እድገት የሚያሳልጡ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን በመግለጽ።
በጥቅሉ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ለዘርፉ ልማት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርኃ ግብር የኢትዮጵያ ተወካይ ቻሩ ቢስት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማስፋት እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የገቢ ምርቶችን በመተካት በድምሩ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ትልቅ አቅም አለው ብለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብርም ዘርፉን ለማጠናከር የፖሊሲ ምክረ ኃሳቦችን በማቅረብ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።