ቀጥታ፡

ሸዋል-ኢድ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ የኢትዮጵያ መልካም ገጽታዎችን የማስተዋወቅ ዕድል ያሰፋል- ባለሙያዎች

ሐረር፤ኅዳር 28/2016 (ኢዜአ)፡- የሸዋል-ኢድ በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳስስ ቅርስነት  መመዝገቡ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ አቅም እንደሚፈጥር  የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ። 

የሸዋል ኢድ በዓል የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዳን ጾም ከተፈታ በስድስተኛው ቀን የሚከበር ሲሆን፤ በዓሉ በተለይ በሐረሪዎች ዘንድ በደመቀ መልኩ ይከበራል።

የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ የሆነው የሸዋል ኢድ አከባበር በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሰሞኑን በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቧል። 

ይህም ሐረርን በድርጅቱ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገሪቱ ከተማ አድርጓታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን እንዳሉት የሸዋል-ኢድ በዓል በድርጅቱ መመዝገቡ ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሀብቶች ዓለም በይበልጥ እንዲያውቀው ያደርጋል።


 

የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ እንዳስረዱት ኢትዮጵያ በበርካታ መስኮች ኅብረ ቀለማት ያላትና ብዝኃነትን የምታስተናግድ ሃገር ናት።

የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር በዩኔስኮ መመዝገቡ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች ቱሪስቶች  እንዲጎበኙት ያደርጋል ብለዋል።

 የሸዋል ኢድ መመዝገብ  በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ከማስተዋወቅ ባለፈ 

የክልሉንም ሆነ የአገርን  መልካም ገጽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።


 

የበዓሉ አከባበር በዩኔስኮ በመመዝገቡ መደሰታቸውን የገለጹት በውጭ ቱሪስት አስጎብኚነት የተሰማሩት አቶ አብዲ አህመድ ናቸው።

 በተለይ የወጭ ጎብኚዎች በዓሉን ለመታደም ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በዓሉ በድርጅቱ መመዝገቡን ተከትሎ በአገር ውስጥ ያሉ አስጎብኚ ድርጅቶች በበዓሉ ለመታደምና ቱሪስቶችን ለማምጣት  ፍላጎት አድሮባቸው ከወዲሁ በዓሉ የሚከበርበትን ጊዜ መጠየቅ  እንደጀመሩ ተናግረዋል።


 

በሐረር ከተማ የቱሪዝም ባለሙያ አቶ ሊሻን ከተማ በበኩላቸው የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ  የሐረሪ ክልል ያላትን እምቅ  ሀብቶች ይበልጥ ለማስተዋወቅ  ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስረድተዋል። 

 ወደ ክልሉ የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር ከመጨመር ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳድገዋል ብለዋል። 


 

"የበዓሉ አከባበር በዩኔስኮ መመዝገቡ በዓሉን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል" ያሉት ደግሞ በክልሉ የሚገኘው የኢናይ አቢዳ ዕደ ጥበብ ኮሌጅ ዲን ወይዘሮ ፈርዶሳ ቶፊቅ ናቸው። 

ድርጅቱ በዓሉን መመዝገቡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አመልክተው፣ ቅርሱን ለትውልድ በማስተላለፍና በማስተዋወቅ ረገድ ሁሉም ወገኖች ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም