ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ከጎረቤት አገራት ጋር አብሮ ማደግን ማእከል ያደረገ ነው- ዶ/ር ፍጹም አሰፋ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 28/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት የአካባቢውን ሃገራት የልማትና የለውጥ ፍላጎት ማእከል ያደረገ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ከሲ.ጂ.ቲ.ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ተሳስራ ለማደግ ፍላጎት ያላት በመሆኑ ወደ ጎረቤት ሃገራት የሚዘልቁ የባቡር እና የመንገድ መሰረተልማት ስትገነባ መቆየቷን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው  የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር  እያደገ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የባህር በርን የተመለከተው ስጋት ግልጽና አሁናዊ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ፍላጎት በጋራ ተጠቃሚነትን ማእከል ያደረጉ ውይይቶችና የሰጥቶ መቀበል ስምምነቶችን እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ሃገራት በመሰረተ ልማት አውታሮች ባለመተሳሰራቸው የሚፈለገውን ያህል እድገትና የሃገራትና የህዝቦች ትስስር እንዳልተፈጠረ በማብራራት ለዚህ ሁለንተናዊ ትስስር መጠናከር  ደግሞ ኢትዮጵያ የሚታዩ ተግባራትን ላለፉት አስርት አመታት ስትተገብር መቆየቷን አስታውሰዋል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የመሰረተ ልማት ትስስርን በእጅጉ የሚፈልግ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፍጹም ይሄንን በማሳካት ሄደት ውስጥ ኢትዮጵያም የድርሻዋን በማበርከት የጥቅሙ ተካፋይ ለመሆን እየሰራች ነው ብለዋል።

ዶ/ር ፍጹም “ሌሎቹን በማራቅና ወደ ሌሎቹ በመቅረብ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሳይሆን ከኢትዮጵያ የለውጥና የልማት ፍላጎት አንጻር በማየት ብቻ ነው ወደ ብሪክስ አባልነት የተገባው” ያሉ ሲሆን “የኢትዮጵያውያንን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር እስከጠቀመ ድረስ መንግስት ከየትኛውም ሃገርና የልማት አጋር አካላት ጋር በትብብር ይሰራል” ሲሉ አስረድተዋል።

“ብሪክስ የራሱ ባንክ በመመስረቱ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት እቅዶቿና ለጋራ ተጠቃሚነት የሚያግዝ ገንዘብ ልታገኝበት ስለምትችል ከቡድኑ ጋር አብራ ትሰራለች” ብለዋል።  

ኢትዮጵያ የአየር ንብርት ለውጥ እያስከተለ ያለውን የአደጋ ተጋላጭነት ለመከላከል ባደረገችው ጥረት ላለፉት አምስት አመታት 32 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞችን መትከሏን የገለጹት ዶ/ር ፍጹም የተፈጥሮ ሃብትን የመንከባከብና አካባቢን አረንጓዴ የማልበስ ሃገራዊ ዘመቻው በአለም ቀዳሚዋ እንደሚያደርጋት አስረድተዋል።

እንደ ዶክተር ፍጹም ገለጻ “ኢትዮጵያ እስካሁን የምታገኘው የታዳሽ ሃይል ሽፋን ከ45 በመቶ ብዙም ያልተሻገረ ሲሆን የሃገሪቱን የሃይል ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ የሆነው የታዳሽ ሃይል አማራጮችን ማስፋት ነው”

ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ትልም ግዙፍ የገንዘብ አቅም እንደሚፈልግ የገለጹት ዶ/ር ፍጹም ይሄ እቅድ እንዲሳካ ካስፈለገ ለአለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማትና ሌሎች የልማት አጋሮች ኢትዮጵያ የተጫናት እዳ ሊቃለልላትና የመክፈያ ጊዜውም ሊራዘም እንደሚገባ መግለጻቸውን አንስተዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም