የመቻራ የግብርና ምርምር ማዕከል ከ20 በላይ የተሻሻሉ የሐረር ቡና ዝርያዎችን በምርምር አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የመቻራ የግብርና ምርምር ማዕከል ከ20 በላይ የተሻሻሉ የሐረር ቡና ዝርያዎችን በምርምር አገኘ
ጭሮ ፤ ሕዳር 28/2016 (ኢዜአ) ፡- የመቻራ የግብርና ምርምር ማዕከል ከ20 በላይ የተሻሻሉና በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የሐረር ቡና ዝርያዎችን በምርምር ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ከማዕከሉ ጋር በመሆን አዳዲስ የቡና ምርት ዘሮችን ከማቅረብ ጎን ለጎን ከየወረዳው ያሉ የቡና ችግኞችን በመሰብሰብ የአካባቢውን አየር የመላመድ ስራውን እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል፡፡
የምርምር ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቀደ ገመቹ እንዳሉት፤ የሐረር ቡና ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ ካሉ የቡና ዝርያዎች ከቀዳሚዎቹ የሚመደብ ነው።
የቸኮላት ቃና ያለው የሐረር ቡና በዓለም ገበያ ተወዳጅ የነበረ መሆኑን ገልጸው፤ አርሶ አደሩም ሆነ የግብርና ባለሙያዎቹ የቡናው ጣዕምና በገበያ ተፈላጊነት ጠብቆ ለማቆየት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ይበልጥ ተወዳጅ የሆነውን የቡና ምርትን ለማቅረብ ማዕከሉ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ትኩረቱን በቡና ምርምር ላይ አድርጎ መቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡
ማዕከሉ እስካሁን ባደረገው ጥረት ከ20 በላይ የቡና ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የምርምር ማዕከሉ በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች ሲመረት የነበረውን የሐረር ቡና በምርምር በመታገዝ በተሻሻሉና በአጭር ጊዜ ምርት በሚሰጡ አዳዲስ የቡና ምርጥ ዝርያዎች በመተካት ለአርሶ አደሩ በማቅረብ እንደሚገኝ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ሞካ፣ ቡልቱም፣ አሩዛና መቻራ አንድ የተባሉ አራት ዓይነት የማዕከሉ የምርምር ውጤት የሆኑ የተሻሻሉና በሽታን መቋቋም የሚችሉ የቡና ዝርያዎችን ለግብርና ጽህፈት ቤቶችና ለአርሶ አደሩ በብዛት ሲያደርሱ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ነባር የቡና ምርት በአምስት እና ስድስት ዓመታት ሲደርስ የነበረውን ዓመቱን በማሻሻል "እነዚህ አዳዲስ ዝርያዎች በሁለት እና ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ምርት እንዲሰጡ ተደርገዋልም" ብለዋል፡፡
የቡናውን የምርት ጥራትና ብዛት ለመጨመር ሲባል በማዕከሉ አቅራቢያ ባሉ እንደ ሶሮሮ፣ ዳሮ ለቡ፣ ቦኬ፣ ሀብሮና መሰላ ባሉ ቀበሌዎች አርሶ አደሩን በማደራጀት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን የማባዛት ስራ በማሰራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርና ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቡሽራ አደም በበኩላቸው፤ በዞኑ የሐረር ቡናን በጥራትና ብዛት የማምረት ስራው በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን የማባዛት ስራውም ማዕከሉ ከጽህፈት ቤታቸው ጋር በመተባበር በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ጭምር እያካሄደ መሆኑን በመልካም ጎኑ አንስተዋል።
አርሶ አደሩን የመከታተልና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ቡና አቅራቢ እንዲሆን ከመቻራ የግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመሆን እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ሁሴን የሱፍ እንዳሉት፤ ከምርምር ማዕከሉ ጋር አዳዲስ የቡና ምርት ዘሮችን ከማቅረብ ጎን ለጎን ከየወረዳው ያሉ የቡና ችግኞችን በመሰብሰብ የአካባቢውን አየር የማላመድ ስራውን እየተከታተሉ ነው።
በመላመድ ስራውም ዝርያው ይበልጥ ምርት የመስጠት አቅሙን የማሳደግ ስራ እንደሚሰራ አክለዋል፡፡
የሐረር ቡና በሽታ መቋቋም እንዲችል በየጊዜው በምርምር የዳበሩ ግንኙነቶችን በማቅረብና ችግኞችም በማባዛት ለአርሶ አደሩ የማዳረስ ስራንም እየሰሩ መሆኑን አክለዋል፡፡
በሶሮሮ አካባቢ ተደራጅተው የቡና ችግኞችን በማባዛት ላይ ካሉ 17 አባላት መካከል አርሶ አደር አልዪ ሁሴን እንደገለጹት፤ ከቡና ልማቱ በፊት በስድስት ዓመት አንዴ የሚደርስና ምርቱም 'አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ' የሚል ነበር። በዚያም ትርፍ ሳያገኙ ረጅም ጊዜ ይቆያል።
በተጨማሪም በበሽታ በተደጋጋሚ መጠቃቱም የሚጠበቀውን ያህል ምርት እንደማያስገኝ አውስተው፤ አሁን ግን ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውንና ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን መጨመሩንም ገልፀዋል፡፡
የመቻራ ግብርና ምርምር ማዕከል ባደረገላቸው የተሻሻለ የቡና ዘር መጠቀማቸው በሁለትና ሶስት ዓመት በብዛትም በጥራትም የተሻለ ቡና ምርት መሰብሰብ እንዲችሉ የረዳቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር አህመድ መዬ ናቸው፡፡
ማዕከሉ አዳዲስ የቡና ምርጥ ዘሮችን እንደ የአካባቢው አየር ንብረት እያቀረበ መሆኑ ጠቁመው፤ በቡና እንክብካቤ ላይ ጥሩ ግንዛቤ እያገኙ በመሆናቸው "አምርተን ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል" ብለዋል፡፡