ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የድርሻችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የድርሻችንን እንወጣለን
ሶዶ፤ህዳር 28 /2016 (ኢዜአ)፡- ለአገራዊ ምክክር ሂደት ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኃይማኖት አባቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
በክልሉ የጋሞ ዞን የኃይማኖት አባት ቀሲስ ደለለ ደምሴ፤ አገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን በማመልከት ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።
ሂደቱን ለማሳካት የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያን ለማሻገር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለው እንደሚያምኑና ለዚህም መሳካት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
በተለይ በኮሚሽኑ አማካኝነት የሚዘጋጁ አገራዊ ምክክር ጥልቅ ውይይት በማድረግ መተማመን ላይ የማድረስ ዕድል ያለው መሆኑን እንደተረዱ ተናግረዋል።
በዚህም የከረሙ ቂምና ቁርሾን ለማስወገድ እንዲቻል ይቅርታና ስምምነትን በማንገስ ሰላም እንዲሰፍን ማመቻቸት እንደሚችል ጠቅሰው፤ ምዕመኑን በዚህ ላይ በማስተማር አርዓያነት ያለው ተግባር በማከናወን የበኩሌን አወጣለሁ ብለዋል።
በኮሬ ዞን የኃይማኖት አባት ጃፋር ኡስማን በበኩላቸው፤ ምክክሩ እንደአገር የምንመኘውን ሁሉአቀፍ ሰላምን ለማስፈን ከወዲሁ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይም ልዩነት አለን ብለው የተራራቁ አካላት ተቀምጠው እንዲነጋገሩ ለማመቻቸት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች የመጨረሻ እልባት ሊያገኙ ይችላሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
እንደ ሃይማኖት አባት ሰላምን መስበክ ዋንኛው ግባቸው በመሆኑ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የእምነቱ ተከታዮችን በማስተማር እገዛ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
አገራዊ ምክክሩ የህብረተሰቡን የመቻቻልና የመከባበር ባህል ለማጠናከር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ የእድር ሰብሳቢ አቶ ደመቀ ጨለሞ ናቸው።
እድር መሠረታዊ ዓላማው ለክፉና ደግ ጊዜያት አስቀድሞ ገንዘብ መሰብሰብ ሲሆን በህብረቱ ውስጥ የተለያየ የሐይማኖትና ብሔር ስብጥር ያለው ነው ብለዋል።
እድሮች ልዩነቶችን ከማቻቻልና አንድነትን ከማስቀጠል አኳያ አይተኬ ሚናቸውን በመወጣት ለምክክሩ ስኬታማነት በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።
ለአካባቢያቸውና አባሉ የምክክር ሂደቱን ግንዛቤ በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ የበኩሌን ለመወጣት እተጋለሁ ነው ያሉት።
በጌዴኦ ዞን የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አየለ ጀቦ በበኩላቸው፤ የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማና ተግባር መደገፍ ሀገር እንድትቀጥል ማድረግ ነው ብለዋል።
የነበሩብንን ችግሮች በውይይትና መግባባት ለመፍታት ነባር እሴቶች ለትውልዱ በማስረፅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ህዝቡ ምክክሩ ነፃና አሳታፊ መሆኑን በመረዳት በሚወክለው አካል እድሉን ተጠቅሞ በመሳተፍ ገንቢ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ከችግሮች መፍቻ ዘዴዎች መካከል አንዱ በሆነው አገራዊ ምክክር የመፍትሄ ሀሳብ በማፍለቅ የኮሚሽኑ ግብ እንዲሳካ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ ለተባባሪ አባላት ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል።