የመደመር ቀን የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር ቀን የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን በማስመልከት የመደመር ቀን የምክክር መድረክ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የ18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ብዝሃነትና እኩልነት፥ ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ኃሳብ ከኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ መርኃ ግብሮች በድምቀት መከበሩን ቀጥሏል።
በዚህም መሰረት ኅዳር-25፣ 26 እና 27 በቅደም ተከተል የወንድማማችነት፣ የብዝኃነትና የአብሮነት ቀናት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት የተከበረ ሲሆን በዛሬው እለት ኅዳር-28 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ "የመደመር ቀን" አስመልክቶ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩም የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የሶማሌ ክልል ምክር-ቤት አፈ-ጉባኤ አያን አብዲ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ ከንቲባዎችን ጨምሮ የፌደራልና የክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።
በመድረኩም "የመግባባት ዴሞክራሲ ጽንሰ ኃሳባዊ ዳራ እና ኢትዮጵያዊ እሳቤ" እንዲሁም "የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትና የሶማሌ ክልል ሕዝብ ተጠቃሚነት ከለውጡ በፊትና በኋላ" የሚሉት ሁለት የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ነው።