ቀጥታ፡

ወጣቱ የጋራ ትርክቶችን  በመረዳት  ለዘላቂ ሰላምና  ሀገራዊ እድገት የድርሻውን እንዲወጣ  እንሰራን- የሀገር ሽማግሌዎች

ሚዛን አማን፤ ኅዳር 28/2016 (ኢዜአ) ፡- ወጣቱ የጋራ ትርክቶችን  በመረዳት  ለዘላቂ ሰላምና  ሀገራዊ እድገት የድርሻውን እንዲያበረክት  የበኩላቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን በማስመልከት በክልሉ የሀገር ሽማግሌዎችን አናግሯል ።

በክልሉ የቤንች ሸኮ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ ሻንቆ ጋኪናንስ  እንዳሉት "ብዝኃ ብሔርና ሃይማኖት ባለበት ሀገር ውስጥ ኢትዮጵያዊነት በአንድነት ጸንቶ ለዛሬ የደረሰው አንድ የሚያደርጉ የጋራ ታሪኮችን ጨምሮ እሴቶችን በመያዝ  መሆኑን መገንዘብ ይገባል" ። 

"የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል  የጋራ ትርክቶችን አጉልቶ በማሳየት አንድነታችንን ማጽናት አለብን" ሲሉም አክለዋል።

"እኛ ያየነውንና ያለፍንበትን የጋራ ታሪክ ለወጣቱ በማሳወቅና በማስተላለፍ ለዘላቂ ሰላምና ልማት የድርሻውን እንዲወጣ የበኩላችንን እናበረክታለን" ሲሉ አቶ ሻንቆ ገልጸዋል ።

እንደ አድዋ ያሉ የጋራ ትርክቶች የህዝቦች አንድነት ቋሚ ምሶሶዎች መሆናቸውን ለአብነት  ያነሱት አቶ ሻንቆ   "ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን በማጽናት የሀገርን ህልውና ማስቀጠል አለብን " ብለዋል።

ለኢትዮጵያ አንድነት የሀገርና የህዝብን የጋራ አጀንዳ አስቀድሞ መሥራት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን የሀገር ሽማግሌ ማለራሻ ደምሴ ቦንጎ ናቸው።

አቶ ማለራሻ እንዳሉት በማያግባቡ ሀሳቦች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ የጋራ እውነትን ላይ መድረስ በየባህሎቻችን ያለ ሀቅ ነው።

"አንዱ ለሌላው መከታና ማረፊያ የሚሆንበት ዕሴትን በመጠቀም ጉዳዮቻችንን  በተረጋጋ ሁኔታ መፍታት  እንጂ አንድ ጫፍ ይዞ መጓዝ  በተለያዩ ጉዳዮች ተጋምዶ ለዘመናት ለኖረው ማህበረሰብ አይጠቅምም" ብለዋል።

"ወጣቱ ትውልድ በሀሰተኛ ትርክት እንዳይደናገርና የጋራ እውነቶችን እንዲያውቅ ከማድረግ አኳያ ማስተማር ይጠበቅብናል " ሲሉም አመልክተዋል። 

ኢትዮጵያዊያን  ከሚለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን በርካታ የጋራ ሀብት፣ ታሪክና ማንነት ያሉን ኩሩ ህዝቦች ነን " ያሉት አቶ ማለራሻ እውነታውን ወጣቱ እንዲያውቀው ለማድረግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የኮንታ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ በላይነህ ዶጮ በበኩላቸው "ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በአንድነት ቆመን ከሰራን ብቻ ነው" ብለዋል ።

"ትላንት አብሮን የነበረውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ማጽናትና መጠበቅ  ከሁላችንም የሚጠበቅ ሥራ ነው" ሲሉም አክለዋል ።

የመመካከርና የመነጋገር ዕሴቶቻችንን እያጎለበትን አንድነታችንን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ አቶ በላይነህ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም