ቀጥታ፡

የዓለም ጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና የትምህርት ማዕከል የመክፈቻ ስነ- ስርዓት እየተካሄደ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2016 (ኢዜአ)፦ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና የትምህርት ማዕከል በአዲስ አበባ የመክፈቻ ስነ- ስርዓት እየተካሄደ ነው።

የማዕከሉ ፅህፈት ቤት ስራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ የአገራት አምባሳደሮችና ሌሎች ዲፕሎማቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮችና እንግዶች በተገኙበ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል ተቀማጭነታቸውን እንግሊዝ ባደረጉ በታሪክ፣ ሕግ፣ ባሕል እና ሌሎች ሙያዎች ሰፊ ልምድ ባካበቱ ጥቁሮች  የተመሠረተ ሲሆን ማዕከሉን ዕውን ለማድረግም ረዘም ያለ ጊዜ ወስዷል።


 

ከቀናት በፊቱም የማዕከሉ መስራች አባላትን የያዘ እና በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለስ የተመራ ልዑክ አዲስ አበባ መግባቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በዚህም ማዕከሉ በዛሬው ዕለት ዋና ፅህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ በይፋ ከፍቷል።

ኢትዮጵያ ምድረ-ቀደምትነቷ፣ የጥቁሮች ቀንዲልነቷ፣ ቅኝ አለመገዛቷ፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሥራችና ማዕከልነቷ፣ ተመራጭ  አድርጓታል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካዊነት ማበብ፤ ለጥቁር ሕዝቦች ከጭቆና ቀንበር እንዲላቀቁ ድጋፍ ማድረጓና የአያሌ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ተመራጭ እንዳደረጋት የማዕከሉ መስራች አባላት ገልፀዋል።

የማዕከሉ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ማድረጉም ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ትግል እና ቅርስ አጠባበቅ ለዋለችው አበርክቶ ዕውቅና የሚሰጥ እና ለሀገሪቷም የጎላ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳው ይኖረዋል ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም