ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2016 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሠረተውን የብሔራዊነት ትርክት የምንገነባበት እንደሚሆን እምነቴ ነው ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለ18ኛ ጊዜ ‹ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት› በሚል ርእስ በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ በጅግጅጋ እየተከበረ ነው፡፡

መሪ ቃሉ እንደሚያመለክተው ይህ በዓል የኢትዮጵያዊነት በዓል ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ማለት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማዕከል ያደረገ ሀገራዊ ማንነት በመሆኑ፡፡

ኢትዮጵያዊነት በአንድ በኩል የብሔር ብሔረሰቦችን ብዝኃነት የሚቀበል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄንን ብዝኃነት አስተሣሥሮ የያዘና ለዘመናት የተሻገረ ጠንካራ አንድነት አለ ብሎ የሚያምን ነው፡፡

ይህ በዓል በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሠረተውን የብሔራዊነት ትርክት የምንገነባበት በዓል እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡

ብሔራዊነት ሀገርን ለመከፋፈልና ለማዳከም ከተገነባው ነጠላ ትርክት የምንወጣበት መንገድ ነው፡፡

ከፖለቲካዊ ታሪካችን ይልቅ ማኅበራዊ ታሪካችንን በማጉላት፣ ከትናንትና ይልቅ በዛሬና በነገ ዕድሎቻችንና ሥራዎቻችን ላይ በመመሥረት፣ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የቆመ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመመሥረት የሚያስችል ገዥ ትርክት ነው፡፡

የብሔራዊነት ትርክት መነሻዎችም ባለቤቶችም ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው፡፡

ሐሳቡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መከራና ፈተና ሳይነጣጥላቸው፣ ለጋራ ዕጣ ፈንታቸው ሲሉ በአንድነት የከፈሉትን መሥዋዕትነት ከማፅናት የሚነሣ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ያልገነባ፣ ለኢትዮጵያ ዋጋ ያልከፈለ፣ ማንም ሕዝብ የለም፡፡

ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በገነቧትና ዋጋ በከፈሉባት ኢትዮጵያ በፍትሐዊነት፣ በእኩልነትና በነጻነት የመኖር መብትም አላቸው፡፡

ኢትዮጵያን ከልመና የማላቀቅና የብልጽግናን መሰረት የመጣል ግዴታም አለባቸው፡፡

ብሔራዊነት ትርክት ይሄን ብዝኃነትና አንድነት ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ትርክት ነው፡፡

ዘመን ተሻጋሪና ሁሉን አሰባሳቢ ኢትዮጵያዊነት መገንባት የምንችለውም በብሔራዊነት ትርክት አማካኝነት ነው፡፡

በዓሉን ስናከብር በዚህ መንፈስ እንደምናከብረው አምናለው። በአሉን ያዘጋጀው የሶማሌ ክልል ምስጋና ይገባዋል። መልካም በዓል ይሁን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ህዳር 28፣ 2016 ዓ.ም

May be an image of 1 person

All reactions:

1515

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም