የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 27/2016 (ኢዜአ)፦  የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ፍሬህይወት ትልቁ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥና የኢኮኖሚ ልማትን ማሳለጥ ያስፈልጋል።

በመሆኑም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን እውን  ለማድረግ በተለይም የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን በመዘርጋትና የዲጂታል አገልግሎትን የማስፋት ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ከዚህ አንጻር የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በማስመልከት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ፍሬህይወት ትልቁ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ በማብራሪያቸው ተቋሙ ለመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ዘርፈ-ብዙ የሕዝብ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ዲጂታል አሠራርን በማስፋት የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችል የትራንስፖርት፣ የተሽከርካሪ ሰሌዳ፣ የመንጃ ፈቃድና ሌሎችም ቀልጣፋና የተሳለጡ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

የተሽከርካሪ ሰሌዳ ህትመትን እያከናወነ ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራም  መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2016 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት በነበረው አፈጻጸም ለ60ሺህ ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ አትሞ ማሠራጨቱን ዋና ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።


 

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰለሞን አምባቸው፤ ተቋሙ በተለይም ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር መዘርጋቱን ተናግረዋል። 

በዚህና በሌሎችም አገልግሎቶች ተቋሙ በአዳዲስ አሠራሮች በመታገዝ ግዴታውን በመወጣት የዲጂታል አሠራርን በስፋት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በ2025 ዓ.ም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በመንግሥት ሰፊ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም