ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ እና እውቀት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን

አዳማ፤  ህዳር 27/2016(ኢዜአ) ፦-የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ እና እውቀት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የህግ ምሁራንና ባለሙያዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ እና የህዝቦቿን መፃኢ እድል ከመወሰን አንጻር የባህር በር ማግኘት የህልውና ጉዳይ መሆኑ ስለታመነበት በጉዳዩ ዙሪያ ብዙዎች ሃሳባቸውን እያጋሩ ይገኛሉ።

ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኢዜአ ከህግ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር ቆይታ ያደረገ ሲሆን በምላሻቸውም ጉዳዩ መነሳቱ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የህግ ባለሙያው አቶ ወንድሙ ኢብሳ፣ የባህር በር ጥያቄው "ለረጅም ዓመታት ምላሽ ሳያገኝ የቆየ የኢትዮጵያዊያን አንኳር ጉዳይ ነው" ይላሉ።


 

ይህም በመሆኑ ጥያቄው ወቅታዊና ትክክለኛ እንደሆነ ጠቅሰው ከታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባህር በር ባለቤትነትና መብት ጋር አያይዞ ጉዳዩን በአግባቡ ማስኬድ ይገባል ብለዋል።

''ጥያቄው አብሮ ከመልማትና አብሮ ከማደግ አንጻር መነሳቱ በሁሉም የሚደገፍና ፍትሃዊ ነው'' ሲሉም ያስረዳሉ።

ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በተለይም የሕግ ምሁራንና ባለሙያዎች ከመንግስት ጎን ቆመው ያለባቸውን ሙያዊና አገራዊ ሀላፊነት መወጣት እንዳለባቸው በማከል።

በጂግጂጋ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር አቶ ሙክታር ኡስማን በበኩላቸው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊና ተፈጥሯዊ መብትን መሰረት ያደረገ መሆኑን በማንሳት የአቶ ወንድሙን ሀሳብ ይጋራሉ።

''የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ ምላሽ ማግኘት የሚችል ነው'' ያሉት አቶ ሙክታር፤ በዚህ ረገድ በተለይ የዲፕሎማሲ ስራው መጠናከር እንዳለበት ይመክራሉ።

ከጎረቤት አገራትም ጋር ሰፊ ውይይትና መግባባት መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች ከዚሁ ጎን ለጎን መከናወን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

''የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሙያችን ማገዝ ይገባናል'' ያሉት አቶ ሙክታር፤ በተለይም ተፈጥሯዊ የባለቤትነት መብትን የሚያመላክቱ የጥናትና የምርምር ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከዚህም ባለፈ ከዓለም አቀፍ ህጎች፣ የባህር በር ጥቅምና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላይ ያተኮሩና በተሞክሮ የተደገፉ ስራዎችን ለመንግስት ማቅረብ እንደሚገባም አንስተዋል።

በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የሚከፈለው ዶላር ለሀገራችን ዕድገትና ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበን ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊያንና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማስረዳት ላይ ከመንግሥት ጎን ሆነን መስራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም