ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እና 24ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ከምዝበራ ድኗል -ኮሚሽኑ

ዲላ፤ ህዳር 27/2016(ኢዜአ) ፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እና 24 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ከምዝበራ ማዳን እንደተቻለ የክልሉ ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሶፎኒያስ ደስታ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ሙስና የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እየተሰራ ነው።

በተለይ የሥነ ምግባር ብልሽትን ለማስተካከል ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሌብነትን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  ገልጸዋል።

በክልሉ ባሉ ሁሉም መዋቅሮች ካለፈው ዓመት ጀምሮ የጸረ ሙስና ግብረ ኃይል በማቋቋም በህዝብ ተሳትፎ የተመዘበረ ሃብት የማስመለስና የሕግ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እና 24 ሺህ ካሬ ሜትር የከተማ መሬት ከምዝበራ እንደዳነ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ 130 የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን ተቀብሎ 45 መዝገቦች በክልል ደረጃ፣ የተቀሩትን ደግሞ በዞን ደረጃ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ በበኩላቸው እንደገለጹት በክልሉ ሙስና የሚያደርሳቸውን ውስብስብ ችግሮች በመከላከል ፍትህ እና እውነትን አሸናፊ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በዚህም በየደረጃው የተቋማትን አሰራር በመፈተሽ ክርክሮችን በአግባቡና በገለልተኝነት በመምራት የአሰራር ግልጸኝነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

እንደኮሚሽነሩ ገለጻ ሙስናን በተቀናጀ አግባብ በበቂ መረጃና ማስረጃ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ከሙስና ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ ክሶች በፍርድ ቤቶች በልዩ ችሎት፣ በጥራትና ባጠረ ጊዜ ለመዳኘትም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ሙስናን ለመከላከል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ከጎን ሃብት የማዳንና የሕግ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ አቶ ከፍያለው ገመዴ ናቸው።


 

በዚህም ከመንግሥት ግዥ፣ ከኦዲት ግኝትና መሰል ዘርፎች ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ከብክነት መዳኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም 54 የክስ መዝገቦች በፍርድ ቤቶች ተከፍተው 15 ሰዎች ላይ የፍርድ ውሳኔ መሰጠቱን ኃላፊው አስታውቀዋል።

በክልሉ ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በዲላ ከተማ የጸረ ሙስና ትግል ንቅናቄን በሚያጠናክሩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም