ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መስፈንና ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቆ ለመቀጠል የጋራ ትርክቶችን መገንባት ይገባል -አምባሳደር ብርቱካን አያኖ 

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 27/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መስፈንና ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቆ ለመቀጠል ነጠላ ትርክቶችን በመተው አሰባሳቢ የጋራ ትርክቶችን መገንባት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት"ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት"  በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ያለውን 18ኛውን የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በውይይት አክብረዋል። 

በክብረ በዓሉ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና ሌሎች የተቋማቱ  አመራሮች፣ አምባሳደሮችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል። 


 

አምባሳደር ብርቱካን በመድረኩ ባስተላለፉት መልእክት ሕዳር 29 ቀን ለኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገመንግስታዊ ዋስትና የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት እንዲሁም ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ብዝሃነትና እኩልነትን አስጠብቆ መቀጠል የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች፣ ሚሲዮኖችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እየተከበረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መስፈንና ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቆ ለመቀጠል ነጠላ ትርክቶችን በመተው አሰባሳቢ የጋራ ትርክቶችን መገንባት ይገባል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በስሩ ያሉ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ለእኩልነትና ብዝሃነት መከበር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡና የዲፕሎማሲ ስራውም በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

ቀኑን በማስመልከት የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

18ኛውን የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በመከበር ላይ ይገኛል። 

ሕዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ሕዳር 26 የብዝሃነት ቀን፣ ሕዳር 27 የአብሮነት ቀን፣ ሕዳር 28 የመደመር ቀን እና ሕዳር 29 የኢትዮጵያ ቀን የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን በእያንዳንዱ ዕለት የተለያዩ ሁነቶች በመካሄድ ላይ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም