የምስራቅ፣ የመካከለኛውና የደቡብ አፍሪካ አገራት የቀዶ ጥገና ሐኪሞች አመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 27/2016(ኢዜአ)፦ ከ14 አገራት የተወጣጡ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች የተሳተፉበት የምስራቅ፣ የመካከለኛውና የደቡብ አፍሪካ አገራት የቀዶ ጥገና ሐኪሞች አመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ።

በመድረኩ ላይ "ላይፍ ቦክስ ፋውንዴሽን" የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት "ክሊን ከት" በሚል ስያሜ እየተገበረው በሚገኘው ፕሮግራም ላይ ገለጻ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የቀዶ ህክምናና አንስቴዥያ ፕሮግራም አስተባባሪ አብይ ዳዊት፤ የቀዶ ህክምና ሲታሰብ ዋናው ጉዳይ "ደህንነት" መሆኑን ጠቅሰው ደህንነቱ የተጠበቀና የተሻለ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቀዶ ህክምና አገልግሎት በቅርበት እንዲኖሩ ከማድረግ አኳያም 420 የጤና ተቋማት የቀዶ ጥገና ክፍሎች መገንባታቸውን ተናግረዋል።

በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አቅም የመገንባት ስራም በስፋት መከናወኑን ገልጸው በነዚህ ስራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስታዊ ካልሆነው ላይፍ ቦክስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በተመረጡ ሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጡን የሚያሻሻል "ክሊን ከት" የተሰኘ ፕሮግራም መተግበሩን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ በተለይም የቀዶ ህክምና ያደረጉ ሰዎች በኢንፌክሽን የመጠቃት መጠንን የማሳወቅ እንዲሁም ይህንንም ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች የሚሰሩበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

የላይፍ ቦክስ ፋውንዴሽን የግሎባል ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ትህትና ንጉሴ፤ ፋውንዴሽኑ በቀዶ ህክምና ወቅት የሚያጋጥሙ ኢንፌክሽኖችን ለመቀነስ "ክሊን ከት" የተሰኘ ፕሮግራም ማስጀመሩን አንስተዋል።

በፕሮግራሙ በመታገዝ 10 ሺህ ባለሙያዎችን ማስተማር መቻሉን በመጥቀስ ከዚህ ባለፈ 300 ሺህ የሚጠጉ ህመምተኞችን  ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።


 

በመድረኩ ከ14 አገራት የተወጣጡ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች መሳተፋቸውን የገለጹት ደግሞ በፋውንዴሽኑ የምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም ሃላፊ ሰናይት ቢተው ናቸው።

"የክሊን ከት" ፕሮግራም በኢትዮጵያ ስምንት አመት ማስቆጠሩን በመጠቆም በሆስፒታሎች በቀዶ ህክምና ላይ ያሉ ችግሮችን በመለየት ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

በሰመመን ህክምና ላይ ለአገልግሎት አሰጣጡ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ ለማድረግም ፕሮጀክት ተቀርጾ እየሰተራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም