18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከበረ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 27/2016(ኢዜአ) ፦ 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድምቀት መከበሩ ተገለጸ።
በዓሉ የጅቡቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ መቀመጫቸውን ጅቡቲ ያደረጉ አምባሳደሮች፣ ከተለያዩ አገራት የመጡ የንግድ ማህበረሰብ፣ የኃይማኖት አባቶች እና የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት በተገኙበት “የኢትዮጵያ ምሽት” በሚል በኤምባሲው በድምቀት መከበሩ ተገልጿል።
አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት የብሔር፣ ብሔረሰቦችን ቀን በሁለተኛ ቤታችን ጅቡቲ ከወንድሞቻችን ጋር በጋራ ማክበራችን ክብረ-በዓሉን ልዩ ያደርገዋል።
የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዩሱፍ ሙሳ በበኩላቸው በጂቡቲ እየተካሄደ ካለው 3ኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ኤግዚብሽን ጎን ለጎን ይህ ቀን መከበሩ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ ያላቸውን ወንድማማችነት፣ የጋራ ባህል፣ የንግድ እና የመሰረተ-ልማት ትስስር ይበልጥ የሚያጸና መሆኑን ተናግረዋል።
በዕለቱ ለታዳሚያን የባህላዊ ጭፈራ እና የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶችን በማስተዋወቅ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡