የተለያየ ሃሳብ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን በአገራዊ ምክክሩ በፍትሃዊነት ለማሳተፍ ዝግጅቱ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የተለያየ ሃሳብ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን በአገራዊ ምክክሩ በፍትሃዊነት ለማሳተፍ ዝግጅቱ ቀጥሏል
ሶዶ ፤ ህዳር 27/2016(ኢዜአ) ፦ የተለያየ ሃሳብ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን በአገራዊ ምክክሩ በፍትሃዊነት ለማሳተፍ የሚደረገው ዝግጅት መቀጠሉን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ ለተባባሪ አካላት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንደተናገሩት፤ ዜጎች በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን ሀሳቦች ወደ መድረክ በነጻነት አቅርበው እንዲመክሩ ኮሚሽኑ የማመቻቸት ስራ እያካሄደ ነው።
በማንነት ጥያቄ፣ በፌዴራሊዝም ስርዓት፣ በሰንደቅ ዓላማ፣ በህገ መንግስትና በሌሎችም ያሉ ልዩነቶችን ወደ መድረክ በማምጣት ለመግባባት ምክክር ተደርጎባቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲመጣ ለማስቻል ኮሚሽኑ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ግጭቶችና አለመግባባቶች ተፈጥሯዊ መሆናቸውን ያወሱት ኮሚሽነሩ፤ የተለያየ ሃሳብ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን በአገራዊ ምክክሩ ላይ በፍትሃዊነት ለማሳተፍ የሚደረገው ዝግጅት መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ይህም የቅድመ ዝግጅት፣ የሂደት፣ የትግበራና የክትትል ምዕራፎችን ኮሚሽኑ ለይቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቅድመ ዝግጅቱ ምዕራፍ ከሌሎች ምክክር ካካሄዱ አገራት ልምድ በመውሰድ ለምክክሩ ማመቻቸት አንዱ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።
ከሂደቱ ጋር ተያይዞ ለተባባሪ አካላት ልምድ የማካፋል ስራ መጀመሩን ጠቁመው፤ በችግሮች መነሻ ምክንያትና በመፍትሄ ዙሪያ ህዝቡን ለማወያየት ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
በምክክሩ ችግሮችን በንግግር በመፍታትና መሰረታዊ ለውጦች ለማምጣት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፤ በጉዳዩ ከሁሉም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ውይይት መደረጉንም አውስተዋል።