የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 27/2016(ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ በሲስተም ዝርጋታ፣ በሰው ኃይል ስልጠና እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ አብሮ መስራት የሚያስችላቸው መሆኑም ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እገዛ ለማድረግ እንደሚያስችለው ተጠቅሷል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ኢንጅነር) እና የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ተፈራርመዋል፡፡
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ኢንጅነር) ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ ለዜጎች የሚሰጠዉን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊዉን እገዛ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተቋማቸው የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡