ኢትዮጵያዊነት-በህብር የተሳሰረ አንድነት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊነት-በህብር የተሳሰረ አንድነት

ኢትዮጵያዊነት-በህብር የተሳሰረ አንድነት
ሀገር በጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ እሴት፣ መነሻና መድረሻ ተሳስሮ በተወሰነ ግዛት በሚኖር ህዝብ ይመሠረታል። የሀገርን ትርጉም በሚገባ የተገነዘቡ ሰዎች በቤት ይመስሉታል። አንድን ቤት የሚያቆሙት ማገር፣ ወራጅ፣ ቋሚ እንዲሁም ጣራው በአንድ ላይ ተሰናስለው ነው። ልክ እንደ ቤት ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች፤ ሁሉም ባህሎች፣ ታሪኮችና እሴቶች እያንዳንዳቸው ሰበዝ ሆነው ሲደመሩ አገር ይሆናሉ።
ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ሃያሲ እና የሥነ ጽሑፍ ምሁር ደበበ ሰይፉ “የአክሱም ጫፍ አቁማዳ” በሚል ርእስ በፃፈው ግጥም መደምደሚያው ላይ የሚከተለውን አስፍሯል።
“እኔና ወንድሞቼ ሁላችን . . . ሁላችን፣
ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን፣
ይህ ነው አንድነታችን፣
ይህ ነው ባህላችን፣
ዘመን ማዛጋቱ በያንደበታችን።
በዚህ ግጥም ውስጥ የኢትዮጵዊነት ትርጉም ፍንትው ብሎ ይታያል። የህዝቡ መተዛዘንና መደጋገፍ ምን ያህል ጥልቀት ያለው መሆኑን አጉልቶ ያሳያል።
ገጣሚ ደበበ ሰይፉ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የፃፈው ጹሁፍ ዛሬ ላይ ደርሰን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የመገፋፋትና የመጠላላት አባዜ ስንመለከት ምን ያህል ወደ ኋላ የሚጎትተን አሰተሳሰብ መሆኑን በግልጽ ያመለክታል።
ኢትዮጵያዊነት በህብር የደመቀ፣ በአብሮነት የዘለቀ፣ በጋራ ለመበልጸግ የሚያልምና ነገን አሻግሮ የሚያይ የማህበረሰብ ውጤት ነው፡፡ አባቶቻችን ከወራሪ ጠላት ታግለው የአገራቸውን ነፃነት በደማቸው አስከብረው ለዛሬ ትውልድ ያሸጋገሩት በዚህ መንፈስ ነው። ይህንን ዘመናትን የተሻገረ የጋራ እሴት ለትውልድ ማሸጋገር ከአሁኑ ትውልድ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴቶች ለመጪው ትውልድ ለማሸጋገር ከሚያስችሉ ኩነቶች መካከል አንዱ በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ነው። ይህ ዕለት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ጥቅምና አመለካከት እንዳላቸው በማመን ለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታ ማሰሪያ እንዲሆነን የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነው ህገ መንግስት ያጸደቁበት ነው።
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የጸደቀበትን ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተብሎ መከበር ከጀመረ እነሆ ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ ነው። የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን “ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል።
የዚህ ቀን መከበር የእርስ በርስ ትስስርን ከማጠናከሩም ባሻገር ለብዝሃ ማንነቶች እውቅናን ያጎናጽፋል። በዓሉ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊኖራቸው የሚገባ መስተጋብር በመቻቻል፣ በመከባበርና በመረዳዳት እንዲሁም በፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በህዝቦች እምቅ ባህላዊ እሴቶች የተገነባና ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ እንዲሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተከበረበት ዕለት ባስታለፉት መልእክት “ይህ ቀን የሁላችን ታሪክ፣ የሁላችን ቅርስ የሁላችን እሴት የኢትዮጵያ ሀብትና ኩራት ሆኖ የሚታይበት ሁላችን ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ መሆናችንና በኢትዮጵያ ጥላ ሥር ውበታችን ሞልቶ የሚታይ መሆኑን የምንማርበት ዕለት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ዘንድሮ የሚከበረው የብሔር ብሐረሰቦች ቀን ከህዳር 25 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች እንዲከበር በማድረግ ብዝሃነትን ያማከለ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቶችን ለማጠናከር በሚያስችል እሳቤ እየተከበረ ይገኛል። በዚህም መሠረት ህዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ህዳር 26 የብዝኀነት ቀን፣ ህዳር 27 የአብሮነት ቀን፣ ህዳር 28 የመደመር ቀን እንዲሁም ህዳር 29 የኢትዮጵያ ቀን በሚል መሪ ሐሳብ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
ከላይ የተገለጹት መሪ ሃሳቦች የተለያዩ ግን ደግሞ በይዘት አንድ የሆኑ የወንድማማችነትንና የአብሮነትን እሴቶች የሚያጎሉ ናቸው። ጠለቅ ተብለው ሲታዩ ሁሉም የአንድነትን መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው ሲጠቃለሉም ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ ናቸው።
በዓሉን ለማክበር የተለያዩ ብሄረሰቦች የየራሳቸውን ባህል በቦታው ተገኝተው ለማስተዋወቅ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ በጉዞአቸውም ላይ ባሉ ከተሞችና አካባቢዎች ላይ እይታን በመፍጠር እርስ በርስ ይበልጥ እንዲተዋወቁም ዕድል ይፈጥራል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአብሮነት ይልቅ የተናጠል ተረክ ያነገቡ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች በተለያዩ አካባቢዎች ይስተዋላሉ። በጋራ መኖርን ሳይሆን መገፋፋትን የሚመርጡ፤ በራሳቸው አጀንዳ ሳይሆን በሰዎች አጀንዳ የተገዙ በንጹኃን ደም ፖለቲካ ሰራን ብለው የሚያስቡ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ። ይህን አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑ ቡድኖች በትናትና ላይ የቆሙ፤ ከትናት መላቀቅ ያልቻሉና ነገን ማሰብ የማይችሉ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ልዕልና የሚመነጨው ከእውነትና ፍቅር ነው። ከግራም ከቀኝም ያሉ ዋልታ የረገጡ እሳቤዎች ለኢትዮጵያ የሚበጁ አይደሉም። ኢትዮጵያውያን በዋልታ ረገጥ እሳቤ ለሚፈጠሩ አጀንዳዎች ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የአጀንዳውን ባለቤትና ምንጭ ማወቅ ይጠቅማል። ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን አዳዲስ አጀንዳ እየፈጠሩ ለሚያውኩ አካላት ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነቷን ለማስከበር የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት ይጠበቅበታል። ትናንት ያለፈና ያመለጠ ታሪክ ነውና ትናትን ለመማሪያ ብቻ መጠቀም ከቻልን ነጋችን ያማረ ይሆናል። (በሚስባ አወል)