የትምህርት ጥራትን ማሻሻል የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ማሻሻል የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል - ቋሚ ኮሚቴው
ዲላ፤ህዳር 27/2016 (ኢዜአ):-የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትብብር መስራት እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ የስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
11ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ዐውደ ጥናት "የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ቀውስ ተግዳሮት፣ እድልና የመፍትሄ አቅጣጫ" በሚል መሪ ሐሳብ በዲላ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በዐውደ ጥናቱ ላይ እንዳሉት በኢትዮጵያ ከ30 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘታቸው እድል ቢሆንም የትምህርት ጥራትና ተገቢነት ላይ አሁንም በርካታ ጥረቶች ያስፈልጋሉ።
የትምህርት ስርዓቱን ማሻሻል ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤በዚህ ረገድ የተናበበና የተቀናጀ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና የትውልዱን ሞራል ለመገንባት አዲስ የትምህርት ፖሊስ ወደ ስራ ከማስገባት ባለፈ የዘርፉን ገለልተኝነት እሰከ ማረጋገጥ የደረሱ ማሻሻያዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
በዘርፉ የሚስተዋለውን ስብራት ለመጠገን የሚሰራው ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት በተለይም የዘርፉ ምሁራንና አመራሮች ብዙ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝዋል።
በዐውደ ጥናቱም የትምህርት ስርዓቱን ቀውስ መንስኤዎች በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት ተተግባሪ ሃሳብ ማመንጭት እንደሚገባ በማከል።
ለትምህርት ስርዓቱ መጓደል አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የትምህርት ዘርፉ ተቀዳሚ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ናቸው።
ትምህርት የዩኒቨርሲቲው ዋና ተግባር መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ስርዓቱን ይበልጥ ለማሻሻልም የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ከማድረግ ባለፈ በትምህርት ዘርፍ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራን ነው ብለዋል።
ዐውደ ጥናቱም ለትምህርት ስብራቱ መፍትሄ ከማመላከት በተጓዳኝ ባለድርሻ አካት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ መሆኑን በማውሳት።
በዐውደ ጥናቱ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ክልሎች የትምህርት ዘርፍ አመራሮች፣ ምሁራን፣ የመምሀራን ማህበርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን 10 የሚደርሱ የጥናት ውጤቶች ቀርበው እንደሚመከርባቸውም ታውቋል።