ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበር አንዱ የሌላኛው አለኝታ፣ ጌጥና ውበት መሆኑ በተግባር እየታየበት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 27/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበር አንዱ የሌላኛው አለኝታ፣ ጌጥና ውበት መሆኑ በተግባር እየታየበት መሆኑን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።

18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከሕዳር-25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።

በዚህም መሰረት ሕዳር-25 እና 26 በቅደም ተከተል የወንድማማችነትና የብዝኃነት ቀን በሚል በደማቅ ስነ-ስርአት የተከበረ ሲሆን በዛሬው እለት (ሕዳር-27) ደግሞ የአብሮነት ቀን በሚል በመከበር ላይ ይገኛል።

በጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ ያለውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ዝግጅት በማስመልከትም በዛሬው እለት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የበዓሉ አከባበር በደማቅ ስነ-ስርአት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ቀናትም በተመሳሳይ ሁኔታዎች ይቀጥላል ብለዋል።

የምክክር መድረክና ሲምፖዚየም እንዲሁም የማጠቃለያ ፕሮግራም በማካሄድ በወጣው መርሃ-ግብር መሰረት እንደሚከበር ገልጸዋል።

በጅግጅጋ እየተካሄደ ያለው አከባበር ኢትዮጵያውያን አንዱ የሌላኛው አለኝታ፣ ጌጥና ውበት መሆኑን በተግባር እያሳየ ያለ ሁነት መሆኑንም ተናግረዋል።

18ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በድምቀት ማክበር የሚያስችል ኮሚቴ በማቋቋም ውጤታማ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ አክለውም በዓሉን ተከትሎ በጅግጅጋ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች እንዲሳለጡ ዕድል ማምጣቱን ተናግረዋል።

በክልሉ የዘመናት የህዝብ ጥያቄዎች የነበሩ በተለይም የጤና፣ የትምህርት፣ የመንገድና ሌሎች የልማት ስራዎች ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች የላቀ ስኬት እንደተመዘገበባቸው ገልጸዋል።

18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በቀጣይነትም ሕዳር-28 የመደመር እና ሕዳር-29 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ቀን በሚሉ ስያሜዎች ተከብሮ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም