በቆሻሻ አያያዝ፣ አጓጓዝና አወጋገድ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች በአፋጣኝ ሊስተካከሉ ይገባል- ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ  ፤ ህዳር 27/2016 (ኢዜአ) ፡- በቆሻሻ አያያዝ፣ አጓጓዝና አወጋገድ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን የ2014/2015 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ገምግሟል።


 

የሁለቱን በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ግኝት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ለቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር አቅርበዋል።

በማብራሪያቸውም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በተለይ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ አጓጓዝ፣ አወጋገድ እና  በፕላስቲክ ምርቶች ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ጉድለቶች እንዳሉበት አመላክተዋል።

ከጉድለቶቹ መካከል በገንዳዎች ላይ የሚጠራቀሙ ቆሻሻዎች ሳይነሱ ለረዥም ጊዜ እየተቀመጡ በየአካባቢው የንጽህና መጓደል እያስከተሉና የጤና እክልም እየፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቆሻሻ አወጋገድና የሚያስከትለውን ጉዳት በሚመለከት ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ክፍተትም መኖሩን አንስተዋል።

የአሠራር ሥርዓት በማበጀት ቆሻሻን ወደ ሃብትነት የመቀየር ሥራም በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ ባለመሆኑ እንደ ጉድለት ጠቅሰዋል።

ለደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ ቁጥር 513/1999 እስካሁን ድረስ ደንብና መመሪያ አለማዘጋጀቱም እንዲሁ።

 

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ፤ በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በ1 ሺህ 960 ከተሞች ላይ የተቀናጀ የቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት ለመዘርጋት ታልሞ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም መሠረት እስካሁን በ249 ከተሞች ላይ ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰው፤ በባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ሰበታ እና ሻሸመኔ  ከተሞች ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ  ለመገንባት ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

በሌሎች አሥር ከተሞችም ተመሳሳይ ግንባታዎችን ለማከናወን ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

ከክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ለተመላከቱ ጉድለቶች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም፤ ጉድለቶቹ የተፈጠሩት በበጀት እጥረትና በሰው ኃይል አለመሟላት መሆኑን ተናግረዋል።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 513/1999 አሁን ላይ ወቅቱን የሚመጥን ባለመሆኑ በ2012 ዓ.ም አዲስ ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀ ቢሆንም ፀድቆ ወደ ሥራ ባለመግባቱ በተቋሙ አሠራር ላይ ችግር ስለመፍጠሩ አንስተዋል።

በቀጣይ አዋጁ ፀድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ የመከታተልና ሌሎችም በጉድለት የተነሱ ችግሮችን ለማስተካከል እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ፤ በቆሻሻ አያያዝ፣ አጓጓዝና አወጋገድ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች በአፋጣኝ ሊስተካከሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመሆኑም የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ አጓጓዝ፣ አወጋገድ እና የፕላስቲክ ምርቶች ፈቃድ አሰጣጥ አዋጅ ፀድቆ በአጭር ጊዜ መመሪያ ተዘጋጅቶለት ወደ ሥራ እንዲገባ ባለሥልጣኑ የሚጠበቅበትን ሊሰራ ይገባል ብለዋል። 

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ጥረቶች በማገዝና በመደገፍ ረገድ ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሁም ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም