በደሴ ከተማ አስተዳደር ገበያን ለማረጋጋት በቅንጅት በተሠሩ ሥራዎች ውጤት እየተገኘ ነው-መምሪያው

ደሴ ፤ ህዳር 27/2016 (ኢዜአ) ፡- በደሴ ከተማ አስተዳደር ገበያን ለማረጋጋት በቅንጅት በተሠሩ ሥራዎች ውጤት እየተገኘ መሆኑን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዮናስ እንዳለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት 40 ሚሊዮን ብር በመመደብ ለሸማቹ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ነው።

ለዚህም ባለፉት ወራትም ከ1ሺህ 400 ኩንታል በላይ ጤፍ፣ የዳቦ ዱቄት እና ሌሎች ምርቶች በዩኒየኖችና በሸማች ማህበራት በኩል ለማህበረሰቡ በቅናሽ እንዲቀርቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።


 

እንዲሁም አቅም ያላቸውን ነጋዴዎች በማስተባበር በከተማው ዋና ዋና አካባቢዎች ቦታ ተዘጋጅቶ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ በማድረግ ገበያን የማረጋጋት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በቅንጅት በተሰራው ሥራ ገበያው እየተረጋጋ ከመሆኑ በተጨማሪ በምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን ኃላፊው ገልጸው፤ በቀጣይም ገበያ የማረጋጋት ሥራው እንደሚጠናከር አስታውቀዋል። 

አምስት ሊትር ዘይት ከ680 እስከ 720 ብር፣ አንድ ኩንታል የዳቦ ዱቄት 7ሺህ ብር እና የተለያዩ ሳሙናዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የገበያ ዋጋን ከማረጋጋት ጎን ለጎን ያለአግባብ ዋጋ በጨመሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አቶ ዮናስ ጠቁመዋል።

የቁጥጥር እና የእርምት እርምጃው ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ህገ ወጦችን ከማጋለጥ ባለፈ መንግስት ባመቻቸው የምርት መሸጫ ቦታዎች ተጠቃሚ እንዲሆን አስገንዝበዋል። 

በከተማው በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት እንድሪስ አህመድ በበኩሉ፤ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ዘይት፣ ዱቄት፣ ፓስታና የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያከፋፈለ መሆኑን ተናግሯል።

በተለያዩ ምርቶች ላይ ከ50 ብር ጀምሮ ቅናሽ መኖሩን የጠቆመው ወጣቱ፣ "እንደ ነጋዴ ሁሌም ትርፍን ብቻ ማሰብ ሳይሆን በችግር ጊዜ ከህብረተሰቡ ጎን መቆም ይኖርበታል" ብሏል።

"መንግስት ገበያን ለማረጋጋት እያከናወነ ባለው ሥራ ተጠቃሚ ሆነናል፤ በዚህም ደስተኛ ነን።'' ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ዘሩ አሰፋ ናቸው።


 

የግብርናና የኢንዱስሪ ምርቶችን በቅናሽ እየሸመቱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በመደበኛው ገበያ እስከ 900 ብር ይሸጥ የነበረውን 5 ሊትር ዘይት በ720 ብር፣ ሳሙናና ኦሞም ከመደበኛ ሱቆች በቅናሽ መግዛታቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰዓዳ አህመድ በበኩላቸውበተመቻቸልን የምርት አቅርቦት ተጠቃሚ ነን ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በመደበኛ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ እየተረጋጋ መሆኑን ጠቅሰው በገበያው ዘይት፣ ዱቄት እና ፈሳሽ ሳሙና በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም